በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ነሐሴ 28, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በኬክቺ ቋንቋ ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት በኬክቺ ቋንቋ ወጣ

ዓርብ ነሐሴ 18, 2023 የማዕከላዊ አሜሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሆዜ ሉዊስ ፔኛ የክርስቲያን ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በኬክቺ ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። የመጽሐፍ ቅዱሱ መውጣት የተነገረው በሳን ሁዋን ቻሜልኮ፣ አልታ ቬራፓዝ፣ ጓቴማላ በተደረገው “በትዕግሥት ጠብቁ”! የተባለው የክልል ስብሰባ የመጀመሪያ ዕለት ላይ ነበር። በዕለቱ ለተገኙት 590 ተሰብሳቢዎች የዚህ አዲስ ትርጉም የታተመ ቅጂ የተሰጠ ሲሆን የኤሌክትሮኒክ ቅጂውንና በድምፅ የተዘጋጀውን ቅጂም ማውረድ ተችሏል። በቤሊዝና በጓቴማላ፣ ኬክቺ ቋንቋ የሚናገሩ ከ1,300,000 በላይ ሰዎች አሉ። በአሁኑ ጊዜ በእነዚህ ሁለት አገራት በ17 ጉባኤዎችና 4 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ 520 የኬክቺ ቋንቋ ተናጋሪ አስፋፊዎች አሉ።

ይህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፣ የኬክቺ ቋንቋ ተናጋሪዎች የይሖዋን ቃል በትክክል እንዲረዱ የሚያግዝ መሆኑን የተለያዩ ወንድሞችና እህቶች ተናግረዋል። ለምሳሌ አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “አዲስ ዓለም ትርጉም በ1 ጢሞቴዎስ 1:11 ላይ ይሖዋን ‘ደስተኛው አምላክ’ በማለት ይገልጸዋል። በኬክቺ ቋንቋ የተዘጋጁ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ግን ይህን የይሖዋን ባሕርይ በትክክል አይገልጹትም። አሁን ሰዎችን ሳነጋግር ይሖዋ በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ ደስተኛ እንድንሆን ሊረዳን እንደሚችል ለማስረዳት ይህን ጥቅስ መጠቀም እችላለሁ።”

ይህ አዲስ ትርጉም ቀና ልብ ያላቸው ብዙ የኬክቺ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ ይሖዋን እንዲያውቁትና እንዲወዱት እንዲሁም ለቃሉ አክብሮት እንዲያድርባቸው እንደሚረዳ እንተማመናለን።—ምሳሌ 7:1, 2