የካቲት 26, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቢኖርም የይሖዋ ምሥክሮች ባለፈው ዓመት በደረሱት በርካታ አደጋዎች እርዳታ ሰጥተዋል
ከ2020 የአገልግሎት ዓመት አንስቶ፣ ድርጅታችን እስከ ዛሬ ካከናወነው ሁሉ የላቀ የእርዳታ እንቅስቃሴ እያካሄደ ነው። በዓለም ዙሪያ ከ950 በላይ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል። በ2020 ከወረርሽኙ በተጨማሪ በርካታ አውዳሚ የተፈጥሮ አደጋዎች ተከስተዋል። የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የወጡትን የደህንነት ደንቦች ባገናዘበ መልኩ ለወንድሞቻችን አፋጣኝ እርዳታ ማድረስ ተፈታታኝ ሆኖባቸው ነበር። በእርዳታ እንቅስቃሴው የተካፈሉት ወንድሞችና እህቶች በዚህ ሥራ መካፈላቸው እምነታቸውን እንዳጠናከረላቸው ገልጸዋል። ወንድሞቻችን ካጋጠሟቸው አደጋዎች አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ቀርበዋል፦
አውዳሚ አውሎ ነፋሶች
በ2020 የአገልግሎት ዓመት በወንድሞቻችን ላይ ጉዳት ያደረሱ 126 ኃይለኛ አውሎ ነፋሶች ተከስተዋል፤ ይህም በ2019 የአገልግሎት ዓመት ከተከሰቱት በ11.5 በመቶ ይበልጣል። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ ኃይለኛ የጎርፍ መጥለቅለቅና የመሬት መንሸራተት አስከትለዋል።
ለምሳሌ ፊሊፒንስ በተደጋጋሚ በአውሎ ነፋስ የተመታች ሲሆን በዚህም ምክንያት ብዙ ወንድሞቻችን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
በመላው ናይጄሪያ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ የወንድሞቻችንን ሰብል አውድሞባቸዋል።
በደቡብ ኮሪያ የዝናቡ ወቅት መርዘሙ ከባድ ጉዳት አስከትሏል።
ኃይለኛ ሰደድ እሳቶች
ብዙ አገሮች በሰደድ እሳት ተጠቅተዋል፤ በአንዳንዶቹ አካባቢዎች በታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ሰደድ እሳት ተመዝግቧል።
ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ወንድሞቻችን በሚኖሩባቸው ቦታዎች ከ400,000 ሄክታር በላይ የሚሆን አካባቢን ያጋየ እጅግ በጣም ኃይለኛ እሳት ተከስቷል።
በዩናይትድ ስቴትስ እንዲህ ዓይነት ኃይለኛ ሰደድ እሳቶች ተነስተው ነበር።
በአውስትራሊያ የሚኖሩ ወንድሞቻችንም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸዋል።
የደህንነት ሕጎችን ያከበረና ውጤታማ የሆነ የእርዳታ ሥራ
እነዚህ አደጋዎች በደረሱበት ወቅት ድርጅታችን፣ እርዳታ የሚሰጡ እና የሚቀበሉ ወንድሞቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የደህንነት ደንቦችን አውጥቶ ነበር።
ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ባለ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ እገዛ ያበረከተው ወንድም ሃን ቻን ሂ፣ የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ስለተወሰዱት አንዳንድ እርምጃዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ጠዋት ጠዋት የሁሉንም ሰው ሙቀት እንለካ፣ ምንጊዜም አካላዊ ርቀታችንን እንጠብቅ፣ በቦታው የሚሠሩትን ፈቃደኛ ሠራተኞች ቁጥር እንገድብ እንዲሁም በምግብና በእረፍት ሰዓት አንድ ላይ ላለመሰባሰብ እንጠነቀቅ ነበር። በተጨማሪም ፈቃደኛ ሠራተኞቹ ከሥራ በፊትና በኋላ መሣሪያዎቻቸውን በኬሚካል ማጽዳት ነበረባቸው።”
አንዳንድ ወንድሞቻችን በአደጋዎቹ ምክንያት ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ቤታቸው ወድሞባቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ምዕራባዊ ዳርቻ ሰደድ እሳቶች በተነሱበት ወቅት በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ ያገለገለው ወንድም ክሪስ ሺራ እንዲህ ብሏል፦ “ከቤታቸው ለተፈናቀሉ ወንድሞች ማረፊያ ስናመቻች ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ የደህንነት ደንቦችን ለማክበር እንጠነቀቅ ነበር።”
በብዙ አካባቢዎች፣ የደህንነት ደንቦችና እና የጉዞ እገዳዎች በእርዳታ ሥራው መካፈል የሚችሉትን ሰዎች ቁጥር ይገድቡት ነበር። ናይጄርያ ውስጥ በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ ያገለገለው ወንድም ፊሊፕስ አኪንዱሮ እንዲህ ብሏል፦ “ያጋጠመን ትልቁ ተፈታታኝ ሁኔታ [መንግሥት] የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉ ነበር። በዚህም የተነሳ የምንፈልገውን የሰው ኃይል ማግኘት አስቸጋሪ ሆነብን።”
በደቡብ ኮሪያ በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ ያገለገለው ወንድም ኪም ጁን ህዮንግ ደግሞ የእርዳታ ሠራተኞቹ ስለነበራቸው አመለካከት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የእርዳታ ሥራውን የምናከናውነው ለአምላክ እና ለወንድሞቻችን ባለን ክርስቲያናዊ ፍቅር ተገፋፍተን ስለሆነ ምንጊዜም ሥራችንን ስናከናውን ለሁሉም ሰው ሕይወትና ደህንነት ትልቅ ቦታ እንሰጣለን። በመሆኑም ተጨማሪ ጥንቃቄ ማድረግ ቢጠበቅብንም እንኳ የእርዳታ ሥራውን ያከናወንነው በደስታ ነበር።”
የእርዳታ ሥራው የወንድሞችን እምነት አጠናክሯል
ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም የእርዳታ ሥራው ስኬታማ መሆኑ በሥራው የተካፈሉት ሁሉ በይሖዋ ይበልጥ እንዲተማመኑና እምነታቸው እንዲጠናከር አድርጓል።
ለምሳሌ ያህል፣ ወንድም ሃን የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው የእርዳታ ሥራውን ከ24 ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መጀመር እንዲችል በቂ ፈቃደኛ ሠራተኞች መገኘት መቻላቸው አሳስቦት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የተጨነቅኩት ያለምክንያት መሆኑን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ተገነዘብኩ። በመላው አገሪቱ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቀረቡ። ፈቃደኛ የሆኑት ክርስቲያኖች ከመብዛታቸው የተነሳ አንዳንዶቹን መመለስ ነበረብን።” ወንድም ሃን “ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደነበረ እርግጠኛ ሆኛለሁ፤ ይህን ማወቃችንም በጣም አበረታቶናል” ብሏል።
በሆንዱራስ አውሎ ነፋስ በተከሰተበት ጊዜ በእርዳታ ሥራው የተካፈለው ወንድም ብራድ ቤነር ደግሞ በኋላ ላይ ምን እንደተሰማው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታው ውጥረት የሚፈጥር ቢሆንም ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት ወንድሞቻችን የሚያስፈልጋቸውን ምግብ፣ መጠለያ እና መንፈሳዊ ማበረታቻ አግኝተዋል። ሁለት አውሎ ነፋሶች እና ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ አንድ ላይ ተደምረው እንኳ በድርጅታችን ውስጥ ያለውን ፍቅር ሊያጠፉት እንዳልቻሉ በገዛ ዓይኔ ተመልክቻለሁ።”
ፊሊፒንስ ውስጥ በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ ያገለገለው ወንድም አልኪን ዳያግ እንዲህ ብሏል፦ “የእርዳታ እንቅስቃሴው፣ ይሖዋ ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል እንዲሁም ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልገንን ጥበብ በልግስና እንደሚሰጠን ይበልጥ እርግጠኛ እንድሆን አድርጎኛል።”—2 ቆሮንቶስ 4:7
በእርዳታ ሥራው የተካፈሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎች፣ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች እንዲሁም በርካታ ወንድሞችና እህቶች በትጋት ያከናወኑትን ሥራ እናደንቃለን። የወንድሞቻችን ከፍቅር የመነጨ ድካም እንዲሁም በልግስና ያደረጉት መዋጮ ታይቶ በማይታወቅ መጠን አደጋ በደረሰበት በዚህ ዓመት እርዳታ ለማበርከት አስችሎናል።—1 ተሰሎንቄ 1:3