በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዩክሬናውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ወደ ሌሎች አገራት ተሰደዋል

ሰኔ 9, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የዩክሬን ስደተኞች በሌሎች አገራት ኑሮን እንደ አዲስ ጀምረውታል

የዩክሬን ስደተኞች በሌሎች አገራት ኑሮን እንደ አዲስ ጀምረውታል

ኢሪና ማኩካ አሁን የምትኖረው በቼክ ሪፑብሊክ ነው

የዩክሬን ጦርነት ሲፈነዳ ኢሪና ማኩካ የተባለች ያላገባች እህት በካርኪቭ ወዳለው ባቡር ጣቢያ አመራች። የ46 ዓመቷ ኢሪና አገሪቱን ለቅቃ መውጣቱ የተሻለ እንደሆነ ተሰምቷት ነበር። ባቡር ጣቢያው፣ እግሬ አውጪኝ ብለው በሚሸሹ ሰዎች ተሞልቷል፤ ሰዎች መድረሻቸውን እንኳ ሳያውቁ ነበር ባቡር ላይ የሚሳፈሩት። ኢሪና የተሳፈረችበት ባቡር ጣቢያውን ለቅቆ ሲንቀሳቀስ መስኮቶቹ ሙሉ በሙሉ ተሸፍነው ነበር፤ ይህን ያደረጉት ጥቃት እንዳይሰነዘርበት ለጥንቃቄ ብለው ነው። ኢሪና ባቡሩ ወደ ስሎቫኪያ የሚያቀና መሆኑን ያወቀችው ከጣቢያው ከወጡ በኋላ ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢሪና የምትኖረው አጎራባች በሆነችው በቼክ ሪፑብሊክ ነው፤ ወደ ዋና ከተማዋ ፕራግ የደረሰችው መጋቢት 3, 2022 ነው። የጽዳት ሥራ ያገኘች ሲሆን ከዩክሬን ተሰደው ከመጡ ሁለት እህቶች ጋር በአንድ አፓርታማ ውስጥ ትኖራለች። ኢሪና የቼክ ቋንቋም እየተማረች ነው፤ ላለፉት 20 ዓመታት እንዳደረገችው ሁሉ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈሏን ቀጥላለች።

ኢሪና እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ በሕዝቦቹ ተጠቅሞ እንደሚንከባከበን በገዛ ዓይኔ አይቻለሁ። ይህም እምነቴን በጣም አጠናክሮታል።”

ወደ 23,000 የሚጠጉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጦርነቱን ሽሽት ወደ ሌሎች አገራት ለመሄድ የራሳቸውን ውሳኔ አድርገዋል። በሌሎች አገራት ለመኖር የመረጡት ክርስቲያኖች አንጻራዊ ሰላም ያገኙ ይሆናል። ሆኖም ሥራ፣ ቤትና ሕጋዊ ሰነድ ማግኘት እንዲሁም ልጆቻቸውን አዲስ ትምህርት ቤት ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል፤ በዚያ ላይ ደግሞ አዲስ ቋንቋ መማር ይጠበቅባቸዋል። ሕይወታቸው በተመሰቃቀለበት በዚህ ወቅት መንፈሳዊ ልማዶቻቸውን ይዘው መቀጠላቸውና የአፍቃሪ ወንድሞቻቸው እገዛ እንደ መልሕቅ እንደሆነላቸው ይሰማቸዋል።

አናቶሊ ፔርሲአክ፣ ኦሌና እና አሊና አሁን በሩማንያ እየኖሩ ነው

አናቶሊ ፔርሲአክ፣ ባለቤቱ ኦሌና እና የ17 ዓመት ልጃቸው አሊና በሩማንያ ኑሮን ሀ ብለው ጀምረዋል፤ በሜክሎዬቭ ኦብላስት፣ ዩክሬን የሚገኘው አካባቢያቸው በቦምብ ሲደበደብ መኖሪያቸውን ጥለው ተሰደዱ። ወደ ሩማንያ የሄዱት መጋቢት 6, 2022 ነው። አናቶሊ የሞልዶቫ ዜግነት ስላለው ቤተሰቡን ይዞ በሩማንያ እንዲኖር ተፈቀደለት። ኦሌና፣ በስደት ሌላ አገር መኖር “ዛፍን ከነሥሩ ነቅሎ ወደ ሌላ ቦታ ከማዘዋወር ጋር” እንደሚመሳሰል ተናግራለች።

ይህ ቤተሰብ የሩማንያ ወንድሞች ባደረጉላቸው ድጋፍ የራሳቸው አፓርታማ ማግኘት ችለዋል። በተጨማሪም አናቶሊ እና ኦሌና ሥራ አግኝተዋል፤ አሊናም በዩክሬን ካለው ትምህርት ቤቷ የሚሰጣትን የቤት ሥራ በኢንተርኔት መሥራት ችላለች።

በሩማንያ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ይህ ቤተሰብ የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ፍላጎት በማሟላት ብቻ አልተወሰኑም፤ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውንም ለማሟላት የቻሉትን እያደረጉ ነው። ቤተሰቡ በባዕድ አገር ብቸኝነት እንዳይሰማው ወንድሞችና እህቶች አዘውትረው ይጠይቋቸዋል። ኦሌና እና አሊና JW ላንግዌጅ የተባለውን አፕሊኬሽን በመጠቀም እንዲሁም በአዲሱ ጉባኤያቸው ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር በማገልገል ሩማንያኛ እየተማሩ ነው። አናቶሊ ከልጅነቱ ጀምሮ ሩማንያኛ ይናገራል።

አናቶሊ እንዲህ ብሏል፦ “ከመጀመሪያው አንስቶ የይሖዋን እጅ አይተናል። ድርጅቱ እንዲሁም ወንድሞችና እህቶች የሚያደርጉልን ድጋፍ የይሖዋን ፍቅር እንድናጣጥም አስችሎናል።”

ቭላዲስላቭ ሃቨርሉክ እና እናቱ አሊና በፖላንድ አዲስ ሕይወት ጀምረዋል

አሊና ሃቨርሉክ ከጦርነቱ በፊት ባለቤቷን በሞት አጥታለች፤ እሷና የ16 ዓመቱ ልጇ ቭላዲስላቭ ከቪኒትሲያ፣ ዩክሬን ተነስተው ስዋኪ፣ ፖላንድ የደረሱት የካቲት 27 ነበር። አሊና እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ እኔና ልጄ የት እንደምንኖርና ራሳችንን እንዴት እንደምናስተዳድር ግራ ገብቶኝ ነበር፤ ያም ቢሆን ይሖዋ እንደሚንከባከበን እርግጠኛ ነበርኩ።”

የ37 ዓመቷ አሊና ወዲያውኑ ሥራ ማፈላለግ ጀመረች፤ በእርግጥ የምትፈልገው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የሚያስችላት ሥራ ነበር። በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የጽዳት ሥራ አገኘች። “ዋናው ነገር ይህ ሥራ በአገልግሎት ለመካፈልና ቤተሰቤን ለማስተዳደር የሚያስችለኝ መሆኑ ነው” ብላለች።

አሊና እና ቭላዲስላቭ ፖላንድኛ እየተማሩ ሲሆን በዚሁ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ላልተወሰነ ጊዜ ረዳት አቅኚ ሆነው እያገለገሉ ነው። ቭላዲስላቭም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ቀጥሏል።

ዩክሬናውያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በጣም ከባድ ፈተናዎችና ለውጦች እያጋጠሟቸው ነው፤ ሆኖም ይሖዋ ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል እየሰጣቸው ነው። በ2 ቆሮንቶስ 4:8 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በሕይወታቸው ሲፈጸም ተመልክተዋል፤ ጥቅሱ “በየአቅጣጫው ብንደቆስም መፈናፈኛ አናጣም፤ ግራ ብንጋባም መውጫ ቀዳዳ አናጣም” ይላል።