በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ በጀርመን፣ በሜክሲኮ እና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ አስፋፊዎች

መስከረም 14, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የይሖዋ ምሥክሮች በድጋሚ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ጀመሩ

የይሖዋ ምሥክሮች በድጋሚ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ጀመሩ

መስከረም 1, 2022 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች፣ መታወቂያቸው የሆነውን ከቤት ወደ ቤት የሚከናወን አገልግሎት እንደገና በደስታ ጀምረዋል። በዚህ ወር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የሚያደርጉት ልዩ ዘመቻ ደግሞ ደስታቸውን ድርብ አድርጎታል። ለአንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ከቤት ወደ ቤት መስበክ የሚወዱትና የለመዱት የአገልግሎት ዘርፍ ነው። ሌሎች ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ይዘው ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው። በዓለም ዙሪያ በ2023 የአገልግሎት ዓመት መጀመሪያ ላይ ያጋጠሙ አስደሳች ተሞክሮዎች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል።

ጀርመን

መስከረም 2, 2022 ኒኮልና ቲና የተባሉ ሁለት እህቶች በፒተርስሃገን፣ ሰሜን ራይን ዌስትፓሊያ ባለ አፓርትመንት ላይ ከቤት ወደ ቤት እያገለገሉ ነበር፤ ሆኖም ማንንም አላገኙም። አፓርትመንቱን ለቀው እየሄዱ ሳለ አንዲት ወጣት ከኋላ ስትጠራቸው ሰሙ። ሴትየዋ በሯን ባንኳኩበት ወቅት መክፈት እንዳልቻለች ከገለጸች በኋላ ወደ ቤቷ ተመልሰው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያወያዩዋት ጠየቀቻቸው። እህቶች ወደ ሴትየዋ ቤት ሲገቡ ጠረጴዛ ላይ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ተቀምጦ አዩ፤ መጽሐፍ ቅዱሱ በደንብ ጥቅም ላይ እንደዋለ ያስታውቃል። ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱሱን ያገኘችው ከሦስት ዓመት በፊት ጣሊያን ውስጥ ትኖር በነበረበት ወቅት እንደሆነ ነገረቻቸው። በወረርሽኙ ወቅት ወደ ጀርመን ከመጣች ወዲህ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝታ አታውቅም። እህቶች ከሴትየዋ ጋር አድራሻ ከተለዋወጡ በኋላ ስብሰባ ጋበዟት። ከሁለት ቀናት በኋላ ሴትየዋ ሁለት ልጆቿን ይዛ ወደ ስብሰባ መጣች። ይህችን ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ዝግጅት ተደርጓል።

ጓቴማላ

ማኑዌልና ካሮል ጋስታሉም፣ በማም ቋንቋ ክልል ውስጥ ልዩ አቅኚዎች ሆነው ያገለግላሉ፤ ከቤት ወደ ቤት ሲሰብኩ ያገኟት አንዲት ደግ ሴት ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። ሴትየዋ አምላክ ስም እንዳለው አታውቅም ነበር፤ ስለዚህ ለዘላለም በደስታ ኑር! ምዕራፍ 04 ላይ የሚገኘውን “አምላክ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ መወያየት ጀመሩ። ኢሳይያስ 42:8⁠ን ሲያነቡ ሴትየዋ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ከራሷ መጽሐፍ ቅዱስ በማየቷ በጣም ተደነቀች።

ሴትየዋ መጽሐፍ ቅዱስን መያዝ ብቻ በቂ እንዳልሆነ መገንዘቧን እያለቀሰች ተናገረች፤ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በሕይወቷ ተግባራዊ ለማድረግ መማር እንደሚያስፈልጋት ገለጸች። ምዕራፉን ከጨረሱ በኋላ ሴትየዋ በተማረችው ነገር በጣም መደሰቷን ነገረቻቸው። የተማረችውን ነገር ለባለቤቷ እንደምትነግረው ገለጸች። ማኑዌልና ካሮል ከሴትየዋ ጋር በቀጣይነት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል።

ጃፓን

ወንድም ኑካሞሪና ባለቤቱ፣ ዮኮሃማ ውስጥ እያገለገሉ ሳለ በኢንተርኮም አማካኝነት አንዲት ሴት አነጋገሩ። ራሳቸውን ካስተዋወቁ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ነገሯት። እሷም በሩ ጋ እንዲጠብቋት ነገረቻቸው። ብዙም ሳይቆይ ሴትየዋ በሩን ከፍታ “የይሖዋ ምሥክሮች ይመጣሉ ብዬ ስጠብቅ ነበር” አለቻቸው።

ሴትየዋ ናጋሳኪ እያለች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና እንደነበር ነገረቻቸው። በወረርሽኙ ወቅት ወደ ዮኮሃማ ብትመጣም ጥናቷን በዙም ቀጥላ ነበር። በዚያ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አስጠኚዋ “መስከረም ውስጥ ዘመቻ አለ። የይሖዋ ምሥክሮች በእርግጠኝነት ቤትሽ ይመጣሉ። ቤትሽን ሲያንኳኩ መጽሐፍ ቅዱስን በአካል እየመጡ እንዲያስጠኑሽ ጠይቂያቸው” አለቻት። የይሖዋ ምሥክሮች ቤቷ ወዲያውኑ ከተፍ ማለታቸው ሴትየዋን በጣም አስገረማት። ሴትየዋ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንደምትፈልግ የገለጸች ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናትም ቀጠሮ ያዙ።

በጃፓን ያሉ አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ

ሜክሲኮ

አንድ ባልና ሚስት አንዲትን ሴት መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ሲጋብዟት ከበርካታ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና እንዲያውም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ትገኝ እንደነበር ነገረቻቸው። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደተጠፋፋችና አኗኗሯም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ እነሱን መፈለግ እንዳሳፈራት ገለጸች። ይህን ካለች በኋላ አለቀሰች። ባልና ሚስቱ መዝሙር 10:17⁠ን አነበቡላትና ይሖዋ እንዳልረሳት ነገሯት። በይሖዋ መሥፈርቶች መሠረት ለመኖር የምትፈልግ መሆኑ በራሱ የሚያስመሰግናት እንደሆነ ገለጹላት። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተስማማች ሲሆን የ16 ዓመቱ ልጇም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ እንደሚፈልግ ነገረቻቸው።

ባልና ሚስቱ በማግሥቱ ተመልሰው ሲሄዱ ሴትየዋና ልጇ እየጠበቋቸው ነበር። ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር ምዕራፍ 01 ካጠኑ በኋላ በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ጋበዟቸው፤ እነሱም ተገኙ። ሴትየዋም ሆነች ልጇ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸውንና በስብሰባዎች ላይ መገኘታቸውን ለመቀጠል ቆርጠዋል።

ፖርቶ ሪኮ

በፖርቶ ሪኮ ያሉ ባልና ሚስት ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር ለአንዲት ሴት ሲያበረክቱ

ራሞን ከወረርሽኙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል ምሥራቹን የሚሰማ ሰው ለማግኘት ጸልዮ ነበር። የመጀመሪያውን ቤት ሲያንኳኳ አንዲት ሴት በሩን ገርበብ አድርጋ ከፈተች። ራሞንም ሰላም ካላት በኋላ ራሱን አስተዋወቃት። ምሥራቹን መናገር ከመጀመሩ በፊት ሴትየዋ “ምን ያህል በጉጉት ስጠብቃችሁ እንደነበር አታውቅም። ወደ ቤቴ እንድትመጡ ስጸልይ ነበር” አለችው።

ሴትየዋ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝታ እንደነበርና በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኝታ እንደምታውቅ ነገረችው። ሆኖም አካባቢዋን ስለቀየረች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተጠፋፋች። ራሞን ከቤት ወደ ቤት የምናከናውነው አገልግሎት በወረርሽኙ ወቅት ተቋርጦ እንደነበር አብራራላት። ከዚያም መዝሙር 37:29⁠ን አነበበላትና መጽሐፍ ቅዱስን ስለምናስጠናበት ዝግጅት ገለጸላት። ሴትየዋም ግብዣውን በደስታ ተቀበለች። ራሞን አንዲት እህት ሄዳ እንድትጠይቃት አመቻቸ።

ራሞን “ይሖዋና መላእክት ምሥራቹን መስማት ወደሚፈልጉ ሰዎች እንደሚመሩን ተመልክቻለሁ” ብሏል።

ዩናይትድ ስቴትስ

ካትሊን ቶምፕሰን በኬንተኪ ከቤት ወደ ቤት እያገለገለች ነበር፤ ወደ አንድ ቤት ስትቀርብ የፖስታ ሣጥኑ ላይ ጥቅሶች እንደተጻፉና ግቢው ውስጥ “ኢየሱስ ይወድሃል” የሚል ትንሽ ምልክት እንደተቀመጠ አስተዋለች። ካትሊን በሩን ስታንኳኳ አንዲት ሴት ከፈተች። ካትሊን ራሷን ካስተዋወቀች በኋላ በኮቪድ-19 የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት መስበክ አቋርጠው እንደነበር ገለጸችላት። በተጨማሪም በወረርሽኙ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ደብዳቤ በመጻፍና ስልክ በመደወል ሰዎችን ያበረታቱና ያጽናኑ እንደነበር ጠቀሰችላት። ከዚያም ስለ ሴትየዋና ስለ ቤተሰቧ ደህንነት ጠየቀቻት። ሴትየዋም በወረርሽኙ ወቅት አባቷ እንደሞቱባት ነገረቻት። “ደብዳቤዎቻችሁ ይደርሱኝ ነበር። ሳነባቸውም አምላክ የሚያስፈልገኝን ነገር በሚያስፈልገኝ ጊዜ እንደሰጠኝ ይሰማኝ ነበር” አለቻት። ካትሊን ሴትየዋ ባጋጠማት ነገር እንዳዘነች ከገለጸችላት በኋላ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር ምዕራፍ 02 አወያየቻት። በምዕራፉ ላይ ያሉትን ጥቅሶች አነበቡ፤ በተለይ ደግሞ ስለ ትንሣኤ ተስፋ በደንብ ተወያዩ። በዚህ ጊዜ ሴትየዋ ማልቀስ ጀመረች። አባቷ ከሞቱ የዚያን ዕለት ልክ ዓመታቸው እንደሆነ ነገረቻት። ሴትየዋ ለካትሊን አድራሻዋን የሰጠቻት ሲሆን ሌላ ጊዜ መጥታ እንድትጠይቃትም ተስማማች። በኋላ ላይ ደግሞ ለካትሊን “አመሰግናለሁ፤ ዛሬ በጣም የሚያስፈልገኝን ማበረታቻ ሰጥተሽኛል” የሚል የጽሑፍ መልእክት ላከችላት።

ይሖዋ ከቤት ወደ ቤት የሚከናወነውን አገልግሎት እንደገና ለመጀመርና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር የምናደርገውን ጥረት እንደባረከው ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ ጥረቶች የሚያስገኙትን ውጤት ለማየት እንጓጓለን!—ዮሐንስ 4:35

 

ባሃማስ

ካሜሩን

ፓናማ

ፊሊፒንስ

ደቡብ ኮሪያ

ዩናይትድ ስቴትስ