ሐምሌ 23, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን መጠራት ከጀመርን ዘጠና ዓመት ሞላን
እሁድ፣ ሐምሌ 26, 1931 በወቅቱ የዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት የነበረው ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ በኮለምበስ፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለተገኙት ከ15,000 የሚበልጡ ሰዎች ንግግር አቅርቦ ነበር። የስብሰባው የተወሰነ ክፍል በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከ450 በላይ የሬዲዮ ጣቢያዎች ተላልፏል፤ አንድ የሬዲዮ ፕሮግራም በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከፍተኛ ብዛት ያላቸው ጣቢያዎች ሲሰራጭ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር። በስብሰባው ላይ ወንድም ራዘርፎርድ “አዲስ ስም” የሚል ታሪካዊ የአቋም መግለጫ አንብቦ ነበር። የአቋም መግለጫው “የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም በደስታ የምንቀበል ከመሆኑም በላይ በዚህ ስም ለመታወቅና ለመጠራት እንፈልጋለን” የሚለውን ሐሳብ ይዞ ነበር። (“ የአቋም መግለጫው” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) አድማጮቹ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “አዎ!” የሚል መልስ ከሰጡ በኋላ አዳራሹ በጭብጨባ ተናጋ።
የሕይወት ታሪኩ በ1986 የወጣው ወንድም አርተር ዋርዝሌ በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር “በስብሰባው አዳራሽ ከዳር እስከ ዳር ያስተጋባው ጭብጨባ ፈጽሞ ከአእምሮዬ አይጠፋም” ብሏል።
በሌሎች አገሮች የሚኖሩ አንዳንዶች የአቋም መግለጫው ሲነበብ በሬዲዮ ተከታትለው ነበር። በአውስትራሊያ የሚኖሩት ወንድም ባርበርና ባለቤቱ “በአሜሪካ ያሉት ወንድሞች ሲያጨበጭቡ በሜልቦርን ያሉ ወንድሞችም ከመቀመጫቸው ተስፈንጥረው በመነሳት አጨብጭበዋል” በማለት ተናግረዋል። በጃፓንም ጥቂት ወንድሞችና እህቶች የአቋም መግለጫውን አዳምጠው ነበር። ከእነሱ መካከል አንዷ የሆነችው እህት ማትሱኤ ኢሺ ከጊዜ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “በአሜሪካ ካሉት ወንድሞቻችን ጋር አብረን የደስታ ጩኸት አሰማን።”
ስብሰባው በተካሄደበት በኮለምበስ፣ ኦሃዮ የነበሩ የንግድ ቤቶች ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ለመቀበል የሰቀሏቸውን ምልክቶች በመቀየር “የይሖዋ ምሥክሮች፣ እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚሉ ምልክቶችን ሰቀሉ። ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ስለ ትላልቅ ስብሰባዎች ለመዘገብ የሚያወጣው ዘ ሜሴንጀር የተባለ ጋዜጣ በሐምሌ 28, 1931 እትሙ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ ይዞ ወጣ።
ስብሰባው ከተካሄደ ብዙም ሳይቆይ የዓለም ተስፋ የሆነው መንግሥት (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቡክሌት ለማበርከት ትልቅ የስብከት ዘመቻ ተካሄደ፤ ይህ ቡክሌት አዲሱ ስማችን የተዋወቀበትን የአቋም መግለጫ ይዞ ነበር። በሁለት ወር ተኩል ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ቡክሌቶች ተሰራጭተዋል፤ ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ በሃይማኖት መሪዎች፣ በመንግሥት ባለሥልጣናት እና በታዋቂ ነጋዴዎች እጅ ገብተዋል።
ወንድም ማርቲን ፖትጺንገር ስለዚያ ጊዜ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ‘ወደ ቤታችሁ የመጣሁት የይሖዋ ምሥክር ስለሆንኩ ነው’ ስንላቸው በጣም ይገረሙ ነበር። ይህን ሲሰሙ፣ ወይ ራሳቸውን ይነቀንቃሉ ወይም ‘ግን አሁንም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ናችሁ አይደል?’ ብለው ይጠይቁናል።” (“ የይሖዋን ስም የሚያስተዋውቁ ካርዶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ሆኖም ወንድም ፖትጺንገር ከዓመታት በኋላ ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታው በእጅጉ ተለውጦ ነበር! ገና ምንም ነገር ሳልናገር ሰዎች ‘የይሖዋ ምሥክር ነህ አይደል?’ ብለው ይጠይቁኛል።”
ወንድም አሌክሳንደር ሂዩ ማክሚላንም በ1931 በተካሄደው ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ነበር፤ አዲሱ ስማችን በጣም ተስማሚ የሆነው ለምን እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ግሩም ስም እንደሆነ ይሰማኛል፤ ምክንያቱም ይህ ስም የምናከናውነውን ሥራ እና ዓላማችንን ለዓለም ያሳውቃል። ከዚያ በፊት የምንጠራው ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች’ በመባል ነበር። ለምን? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስለነበርን ነው። በሌሎች አገሮች ያሉ ሰዎች አብረውን መጽሐፍ ቅዱስን መማር ሲጀምሩ ደግሞ ‘ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች’ ተብለን መጠራት ጀመርን። አሁን ግን የይሖዋ አምላክ ምሥክሮች ነን፤ ይህ ስም ማንነታችንን እና የምንሠራውን ሥራ ለሰዎች ያሳውቃል።”
በዛሬው ጊዜ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው በመጠራታቸው ይኮራሉ።—ኢሳይያስ 43:10-12