በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የዳኻው ማጎሪያ ካምፕ መታሰቢያ ሕንፃ እና ለፕሬዚዳንት ፑቲን የተላከው ክፍት ደብዳቤ

ሰኔ 2, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የዳኻው ካምፕ የቀድሞ እስረኞች ማኅበር የሩሲያ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን ማሳደዱን እንዲያቆም ጠየቀ

የዳኻው ካምፕ የቀድሞ እስረኞች ማኅበር የሩሲያ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን ማሳደዱን እንዲያቆም ጠየቀ

የዳኻው ማጎሪያ ካምፕ የቀድሞ እስረኞች የመሠረቱት ላገርገማይንሻፍት ዳኻው የተባለው ማኅበር የሩሲያ ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚያደርሱትን ስደት እንዲያቆሙ ጠይቋል። ማኅበሩ ግንቦት 16, 2021 ለፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በላከው ክፍት ደብዳቤ ላይ ሩሲያ በወንድሞቻችን ላይ ጭቆና ማድረሷን አውግዟል።

ደብዳቤው እንዲህ ይላል፦ “መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስለሚያደርሰው ጭቆና በየቀኑ ሪፖርት ይደረጋል።” አክሎም እንዲህ ይላል፦ “የሩሲያ ደህንነት አባላት እና ፖሊሶች የሃይማኖቱን አባላት ቤቶች ገለባብጠው ይፈትሻሉ። የይሖዋ ምሥክሮች አካላዊ ጥቃትና እንግልት ይደርስባቸዋል። በርካታ ወንዶችና ሴቶች የረጅም ዓመታት እስር ተፈርዶባቸዋል። የእስሩን ሁኔታ ለማሻሻል ወይም በአመክሮ ለመፈታት የሚቀርቡ ጥያቄዎች አብዛኛውን ጊዜ ውድቅ ይደረጋሉ።”

ደብዳቤው እንዲህ በማለት ይደመድማል፦ “ሁሉም የሩሲያ ፌዴሬሽን ነዋሪ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የአምልኮ ነፃነቱ እንዲከበርለት እንጠይቃለን። እባክዎ ይህ ግፍ እንዲቆም ያድርጉ!”

እስከ ግንቦት 2021 ድረስ ሩሲያ ውስጥ በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ 61 የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። ከእነዚህ መካከል አረጋውያን ይገኙበታል፤ ለምሳሌ የ70 ዓመቷ እህት ቫለንቲና ባራኖቭስካያ የሁለት ዓመት እስር ተበይኖባት በአሁኑ ወቅት እስር ቤት ትገኛለች። ሐምሌ 2020 አንጎሏ ውስጥ ደም ፈስሶ ነበር። ፍርድ ቤቱ እሷ እና ልጇ ሮማን ባራኖቭስኪ ያቀረቡትን ይግባኝ ግንቦት 24, 2021 ውድቅ አድርጓል፤ ወንድም ሮማን ባራኖቭስኪ የስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶበት ወህኒ ይገኛል።

የፍትሕ ጉዳይ የሚያሳስባቸው ሰዎች በሩሲያ ባሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የሚደርሰው ግፍ እንዲቆም በይፋ የሚያደርጉትን ጥሪ እናደንቃለን። ይዋል ይደር እንጂ ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚያድን እናውቃለን።—ዳንኤል 12:1