ጥር 26, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የድምፅ መግለጫዎች የክልል ስብሰባዎች ለዓይነ ስውራንና የማየት ችግር ላለባቸው ሰዎች ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆኑ አድርገዋል
ዓመታዊ የክልል ስብሰባችን ዘንድሮ ለሦስተኛ ዓመት የድምፅ መግለጫዎችን ያካተተ ይሆናል። የድምፅ መግለጫ ያላቸው ቪዲዮዎች፣ የሚታየውን ነገር የሚያብራራ መግለጫ ያላቸው ሲሆን በዋነኝነት የሚዘጋጁት ለዓይነ ስውራንና የማየት ችግር ላለባቸው ሰዎች ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የድምፅ መግለጫዎችን በቀጣይነት የሚያዘጋጁት በዓለም ላይ ላሉት 43 ሚሊዮን ገደማ ዓይነ ስውራንና 295 ሚሊዮን ገደማ የማየት ችግር ያለባቸው ሰዎች መንፈሳዊ ምግቦችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ነው።
የድምፅ መግለጫዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የድምፅ መግለጫዎች አዘገጃጀት እውቅ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ጆኤል ስናይደር የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያደርጉት ጥረት ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ተደራሽነትን a ለማስፋፋት ያከናወኑት ሥራ በጣም አስደንቆኛል። ቪዲዮዎችን በድምፅ መግለጫዎች አማካኝነት ለዓይነ ስውራን ተደራሽ ማድረግ ብዙዎች የማያስቡት ነገር ነው። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን በማድረጋቸው ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ።”
የበላይ አካሉ በወረርሽኙ ምክንያት የ2020 ዓመታዊ የክልል ስብሰባ በኢንተርኔት አማካኝነት እንዲተላለፍ ሲወስን የድምፅ መግለጫዎችም እንዲካተቱ ተወሰነ። በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ያለው የትርጉም አገልግሎት ክፍል በ2020 የክልል ስብሰባውን የድምፅ መግለጫዎች አዘጋጀ። በ2021 ሥራው በፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ውስጥ ወዳለው የጽሑፍ ንድፍ ክፍል ተዘዋወረ። የድምፅ መግለጫዎችን የሚያዘጋጀው ቡድን በኢንተርኔት በተካሄደ ሴሚናር አማካኝነት ውጤታማ የድምፅ መግለጫዎችን ማዘጋጀት ስለሚቻልበት መንገድ ሥልጠና ወሰደ።
ዶክተር ስናይደር “ሰዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ መግለጫ እንዲሰጡ ማሠልጠን ይቻላል” ብለዋል። ይህም “አጭር፣ ግልጽና በምናብ ለመሣል የሚያመቹ ቃላትን መጠቀምን” እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
የድምፅ መግለጫዎችን የሚያዘጋጀው ቡድን አባላት ለአንድ የክልል ስብሰባ ቪዲዮ የድምፅ መግለጫ በሚያዘጋጁበት ጊዜ በመጀመሪያ ምስሉን ሳያዩ ድምፁን ብቻ ያዳምጣሉ፤ ይህም ዓይነ ስውራን ወይም የማየት ችግር ያለባቸው ሰዎች ቪዲዮውን ሲሰሙ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጥርባቸው ለማወቅ ያስችላቸዋል። እያንዳንዱ የቡድኑ አባል ድምፁን ብቻ ሲሰማ ምን ምስል እንደፈጠረበት ይጽፋል። ከዚያም የቡድኑ አባላት ቪዲዮውን በድጋሚ ያጫውታሉ፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ ቪዲዮው ላይ በገጸ ባሕርያቱ ንግግር መካከል ያለውን ክፍተት ለማስተዋል ይሞክራሉ፤ ምክንያቱም የድምፅ መግለጫዎቹ የሚገቡት ክፍተቶቹ ውስጥ ነው።
የድምፅ መግለጫዎች በሚዘጋጁበት ጊዜ መግለጫዎቹን በገጸ ባሕርያቱ ንግግር መካከል ማስገባት ቀላል አይደለም። በይሖዋ ምሥክሮች የድምፅ መግለጫዎች አዘጋጅ ቡድን ውስጥ የሚያገለግለው ማይክል ሚለን እንዲህ ብሏል፦ “ያለው ክፍተት ውስን ስለሆነ ቪዲዮውን ለመረዳት በጣም አስፈላጊ የሆነው መረጃ የትኛው እንደሆነ መወሰን ይጠበቅብናል። ጊዜውን፣ ቦታውን፣ የተዋንያኑን ሁኔታ እና የሚታየውን ድርጊት ለመግለጽ እንሞክራለን።”
የድምፅ መግለጫዎችን የሚያዘጋጁት ሰዎች በቪዲዮው ላይ ስለሚታየው ነገር የራሳቸውን አመለካከት እንዳይገልጹ መጠንቀቅ አለባቸው። ዶክተር ስናይደር እይታ በድምፅ ሲገለጽ (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የድምፅ መግለጫ የሚያዘጋጁ ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “አድማጮች መረጃውን ብቻ ሰምተው ምስሉን በራሳቸው ምናብ እንዲሥሉ ዕድል ስጧቸው። ይህም ሲባል ‘ተበሳጭቷል’ ወይም ‘አዝናለች’ ማለት የለባችሁም ማለት ነው። ከዚህ ይልቅ ‘እጁን ጨብጧል’ ወይም ‘እያለቀሰች ነው’ በሉ።”
የድምፅ መግለጫዎችን የሚያዘጋጀው ቡድን ስክሪፕቱን ጽፎ ካጠናቀቀ በኋላ የድምፅ ተቀጂው የድምፅ መግለጫውን ይቀዳል። ተቀጂው በተረጋጋ ድምፅ ሊያነብ ይገባል። ማይክል ሚለን እንዲህ ብሏል፦ “የተቀጂው ድምፅ በቪዲዮው ውስጥ ካሉት ገጸ ባሕርያት ጋር ሊፎካከር አይገባም። ተቀጂው በግለት ወይም በስሜት የሚቀዳ ከሆነ አድማጩ የድምፅ መግለጫውን የተቀዳው ሰው ቪዲዮው ውስጥ ያለ ሌላ ገጸ ባሕርይ እንደሆነ ሊያስብ ይችላል።”
የቴክኒክ ባለሙያዎች የመጨረሻዎቹን ማስተካከያዎች ካደረጉ በኋላ የድምፅ መግለጫዎቹ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች እንዲተረጎሙ ወደ ሁሉም ቅርንጫፍ ቢሮዎች የትርጉም ጥቅል ይላካል። ማይክል እንደተናገረው ቡድኑ ላለፉት ሁለት የክልል ስብሰባ ቪዲዮዎች የድምፅ መግለጫዎችን ሲያዘጋጅ ለእያንዳንዱ ደቂቃ ቪዲዮ ሦስት ሰዓት ገደማ ፈጅቶበታል።
የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይተረጉማሉ። የድምፅ መግለጫዎች በዚህ ቁጥር ውስጥ ባይካተቱም አንዳንዶች የድምፅ መግለጫዎች ራሳቸውን የቻሉ ቋንቋዎች ተደርገው ሊቆጠሩ እንደሚገባ ይሰማቸዋል። ማይክል እንዲህ ብሏል፦ “የድምፅ መግለጫ ለዓይነ ስውራን የተዘጋጀ ቋንቋ ነው ሊባል ይችላል። በቪዲዮው ላይ የሚታየው ምስል በድምፅ ይተረጎማል።”
ይሖዋ በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘት እንዲችሉ ስላደረገ እናመሰግነዋለን!—ኢሳይያስ 65:13
a ተደራሽነት ሲባል አንድ አገልግሎት ወይም ሕንፃ ለአካል ጉዳተኞች አመቺ እንዲሆን ለማድረግ የሚሠራውን ሥራ ያመለክታል።