ጥር 11, 2019
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የ2019 ዓመታዊ ስብሰባ ጎላ ያሉ ገጽታዎች
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 5, 2019 ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባውን በኒውበርግ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ አካሂዷል። ከመደበኛ ስብሰባው በኋላ የበላይ አካሉ አበረታች መንፈሳዊ ፕሮግራም አቅርቧል፤ በቀጥታ ስርጭት የተከታተሉትን ሰዎች ጨምሮ 20,679 ተሰብሳቢዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። የእያንዳንዱ ክፍል ጎላ ያሉ ገጽታዎች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል። a
‘መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ነው’
የስብሰባው ሊቀ መንበር የነበረው ወንድም ጌሪት ሎሽ በማቴዎስ 23:10 ላይ የተመሠረተውን የመክፈቻ ንግግር ያቀረበ ሲሆን መሪያችን ሰው ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል።
ይሖዋ የሚጠቀምበት የእርዳታ አገልግሎታችን
ወንድም ስቲቨን ሌት በደስታ መስጠት ያለውን አስፈላጊነት አብራርቷል። ለጋስ መሆናችንን ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ የእርዳታ አገልግሎቱን መደገፍ ነው። ወንድም ሌት በ2018 እና 2019 የአገልግሎት ዓመት በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የደረሰውን ጉዳትና የተከናወነውን የእርዳታ ሥራ ገለጸ። ከ900,000 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች በእነዚህ አደጋዎች የተጠቁ ሲሆን ከ700 የሚበልጡ የስብሰባ አዳራሾችና ከ15,000 የሚበልጡ የወንድሞቻችን ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ለእርዳታ ሥራ 49.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አውጥተዋል።
ከእርዳታ አገልግሎታችን ጥቅም ያገኙ አስፋፊዎች ከልብ በመነጨ ስሜት የተናገሯቸውን የአድናቆት ቃላት የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በዚህ ክፍል ላይ ቀርበው ነበር።
‘የአምላካችን መልካም እጅ በእኛ ላይ ነው . . . እንነሳና እንገንባ’ | ቪዲዮ
ይህ ቪዲዮ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ወደ 80,000 ገደማ ሕንፃዎች እንዳሏቸው ገልጿል። በተጨማሪም ቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎችን ለመጠገን፣ ለማደስና ለመገንባት የምንጠቀምባቸውን ዘዴዎች ጠቅሷል።
የንብረት ግዢ ታሪክ | ቪዲዮ
ይህ ቪዲዮ ለዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮና ለዋናው መሥሪያ ቤት መሬት በመግዛቱ ሥራ የተካፈሉ ሦስት ወንድሞች ከዓመታት በፊት ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ የሚያሳይ ነው፤ እነዚህ ወንድሞች ማክስ ላርሰን፣ ጆርጅ ካውችና ጊልበርት ናዛሮፍ ናቸው። ሦስቱም ወንድሞች በተለያየ ወቅት በግዢ ሥራ ሲካፈሉ የይሖዋን እጅ በግልጽ ያዩት እንዴት እንደሆነ ተናግረዋል።
አዲስ የግንባታ ፕሮጀክት ታቅዷል | ቪዲዮ
ይህ ቪዲዮ የይሖዋ ምሥክሮች የሚዲያ ሥራቸውን በራማፖ፣ ኒው ዮርክ ወደሚገነባ አዲስ ሕንፃ ለማዛወር እንዳቀዱ አሳውቋል። ቦታው የሚገኘው በዎርዊክ ካለው ዋና መሥሪያ ቤት 3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። ግንባታውን በ2022 ለመጀመርና በታኅሣሥ 2026 ለማጠናቀቅ ታቅዷል። የግንባታ ሥራው በስፋት ሲጀመር በቀን 1,500 ገደማ ፈቃደኛ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ።
ማመልከቻዎችን ለማስገባት የሚረዳ አዲስ ዝግጅት | ቪዲዮ
ይህ ቪዲዮ ከጥር 2020 አንስቶ አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚፈልጉ አስፋፊዎች jw.org ላይ ማመልከቻቸውን በመሙላት ለሽማግሌዎች አካል መላክ እንደሚችሉ ይገልጻል።
JW.ORG ላይ የሚወጡ ኦዲዮ ፋይሎችን ማጫወት የሚቻልበት አዲስ ዘዴ
በjw.org ላይ የሚገኙ የተወሰኑ ኦዲዮ ፋይሎችን በአማዞን አሌክሳ ወይም በጉግል አሲስታንት አማካኝነት ማጫወት ይቻላል።
ከሰሜን የሚመጣ ጥቃት
ወንድም ዴቪድ ስፕሌን በኢዩኤል ምዕራፍ 2 ላይ የሚገኘውን ስለ አንበጣ መንጋ የሚናገረውን ትንቢት የምንረዳበትን መንገድ በተመለከተ የተደረገውን ማስተካከያ ገልጿል። ይህ ማስተካከያ መጠበቂያ ግንብ ላይ ሲወጣ ለማጥናት እንጓጓለን።
ለጥናት በተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅማችሁ መጽሐፍ ቅዱስን አጥኑ
ወንድም ሳሙኤል ኸርድ ኢንተርኔት ላይ የሚገኘው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ (የጥናት እትም) ያሉትን ጥቅሞች ገለጸ። ከዚያም አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ (የጥናት እትም) ከማቴዎስ እስከ ሐዋርያት ሥራ ታትሞ እንደወጣ ተናገረ። አስፋፊዎች በጉባኤያቸው በኩል ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ማዘዝ ይችላሉ።
ብዙ ሥራ ይጠብቀናል!
ወንድም አንቶኒ ሞሪስ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ዋነኛ ኃላፊነት ምሥራቹን መስበክ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገለጸ። ቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎች የበላይ አካሉ የስብከቱን ሥራ እንዲያደራጅና ለይሖዋ ሕዝቦች መንፈሳዊ ምግብ እንዲያቀርብ ያስችላሉ። ወንድም ሞሪስ በኅዳር 15, 1976 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን የሚከተለውን ሐሳብ አነበበ፦ “‘ታላቁ መከራ’ ሲጀምር የስብከቱን ሥራ በመላው ዓለም በከፍተኛ ፍጥነትና ስፋት እያከናወንን መገኘት ይኖርብናል። ጌታ ኢየሱስ ለፍርድ ሲመጣ ለአምላክ ሕዝቦችም እንኳ ድንገተኛ ይሆንባቸዋል፤ ምክንያቱም ጌታ የሚመጣው ሥራውን እያጧጧፉ ባሉበት ወቅት ነው!”
ምን የሚያስፈራን ነገር አለ?
ወንድም ማርክ ሳንደርሰን ኢየሱስ በትንቢት በተናገረው መሠረት የአምላክ አገልጋዮች “በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ” የተጠሉ እንደሚሆኑ እንደማይዘነጉ ገልጿል። (ማቴዎስ 24:9) ሆኖም ወንድም ሳንደርሰን መፍራት ያለብን ሰዎችን ሳይሆን ይሖዋን እንደሆነ አብራራ።—መዝሙር 111:10
በሩሲያ ስደት እየደረሰባቸው ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍርሃታቸውን ማሸነፍ የቻሉት እንዴት እንደሆነ ሲገልጹ የሚያሳይ ልብ የሚነካ ቪዲዮ ታይቷል። ንግግሩና ቪዲዮው ሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች እንዲህ ያለ መንፈስ እንዲኖራቸው አበረታቷቸዋል።
የማመዛዘን ችሎታችሁ በትክክል ይሠራል?
ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን ቃል በቃል ሲተረጎም “ከስካር የጸዳ” የሚል ትርጉም ያለውን ቃል የያዙ ጥቅሶች አብራራ። በተጨማሪም በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ‘የማስተዋል ስሜታችንን በሚገባ መጠበቅ’ (ቃል በቃል “ሙሉ በሙሉ ከስካር የጸዳን መሆን”) ያለውን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል።—1 ጴጥሮስ 1:13
ተልእኮውን ትቀበላላችሁ?
ወንድም ኬነዝ ኩክ የ2020 የዓመት ጥቅስ ‘ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ የሚለው ማቴዎስ 28:19 መሆኑን ገለጸ። ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው እንዲጠመቁ መርዳት ያለውን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል።
እንደ ዓመታዊ ስብሰባ ያሉ መንፈሳዊ ፕሮግራሞች በይሖዋ አገልግሎት በትጋት መካፈላችንን እንድንቀጥል ያነሳሱናል።
a ሙሉው ዓመታዊ ስብሰባ ጥር 2020 jw.org ላይ ይወጣል።