ሚያዝያ 16, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የ2020 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—በአፍሪካ
ፕሮግራሙ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ተሰራጨ
በ2020 የተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ታሪካዊ ነበር። የመታሰቢያው በዓል ፕሮግራም ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በተለያዩ ቋንቋዎች በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ተሰራጭቷል።
ይህ ዝግጅት ከ407,000 የሚበልጡ አስፋፊዎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ሌሎች ሰዎች የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም እንዲከታተሉ አስችሏል። በድምሩ ምን ያህል ሰው ፕሮግራሙን እንደተከታተለ ማወቅ ባይቻልም ፕሮግራሙ በተሰራጨበት አካባቢ የሚኖረው አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ከ150 ሚሊዮን ይበልጣል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ በዓለም ዙሪያ ያሉት አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች የመታሰቢያውን በዓል ያከበሩት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ነው፤ ሆኖም አፍሪካ ውስጥ ያሉ ብዙዎቹ አስፋፊዎች በሚኖሩበት አካባቢ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት ውድ ነው፤ በመሆኑም ወንድሞችና እህቶች ከኢንተርኔት ላይ በቀጥታ ቪዲዮ መመልከት ወይም ማውረድ አይችሉም። በዚህም የተነሳ የበላይ አካሉ የተወሰኑ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከቴሌቪዥንና ከሬዲዮ ጣቢያዎች ጋር በመደራደር የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም በርካሽ ዋጋ እንዲያሰራጩ ፈቃድ ሰጠ።
የመታሰቢያው በዓል ከመከበሩ በፊት 11 ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይኸውም የማላዊ፣ የሞዛምቢክ፣ የሴኔጋል፣ የቤኒን፣ የአንጎላ፣ የካሜሩን፣ የኮት ዲቩዋር፣ የዚምባብዌ፣ የዛምቢያ፣ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ እና የጋና ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከቴሌቪዥንና ከሬዲዮ ጣቢያዎች ጋር በመነጋገር የመታሰቢያው በዓል ንግግር በ16 አገሮች ውስጥ ከ36 ወደሚበልጡ አካባቢዎች እንዲሰራጭ ዝግጅት አደረጉ።
አንጎላ
ስድስት የሬዲዮ ጣቢያዎች የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም በስድስት ቋንቋዎች ማለትም በንያኔካ፣ በኡምቡንዱ፣ በኢቢንዳ፣ በኪምቡንዱ፣ በኪኮንጎና በፖርቱጋልኛ ለማሰራጨት ተስማሙ። እነዚህ የሬዲዮ ጣቢያዎች ፕሮግራማቸውን የሚያሰራጩት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባላቸው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ነው።
የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ
መጽሐፍ ቅዱስን የምታጠና አንዲት ሴት ቤተሰቦቿ የይሖዋ ምሥክሮችን ስለሚቃወሙ የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም ብቻዋን ለመመልከት አስባ ነበር። ሆኖም ንግግሩን ለመመልከት እየተዘጋጀች ሳለ አባቷ ከሳሎን “ስብሰባው ጀምሯል!” ብሎ ጠራት። ወደ ሳሎን ስትገባ ቤተሰቦቿ በሙሉ የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም በቴሌቪዥን ለመመልከት ተሰብስበው በማየቷ ተደነቀች። የዚህች ሴት አሥር የቤተሰብ አባላት የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም ተከታትለዋል።
በሉዌና አቅራቢያ በሚገኝ አንድ መንደር የሚኖር የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “የእኛ ፓስተሮች ምንም እርምጃ አልወሰዱም። እናንተ ግን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም አምላካችሁን ማምለካችሁን ቀጥላችኋል። እኛም ከእናንተ ጋር መቀላቀል እንፈልጋለን!”
ጋና
አንድ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም በችዊ ቋንቋ ለማሰራጨት ተስማማ። ጣቢያው ሰዎች የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም እንዲመለከቱ የሚጋብዝ ማስታወቂያም አስተላልፎ ነበር። ከመታሰቢያው በዓል ፕሮግራም በተጨማሪ ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው? እና አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? የተባሉትን ቪዲዮዎች እንዲሁም ያ አዲስ ዘመን እና ሩቅ አይደለም ያ ጊዜ የተባሉትን የሙዚቃ ቪዲዮዎች አስተላልፏል።
ሴኔጋል
አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ስለ ይሖዋ ሲነገር ነበር። በጣም ደስ ይላል! በእጅጉ እንደተባረክን ተሰምቶናል። ይሖዋ አምላካችን በመሆኑ ኮርተናል!”
አንዲት ሌላ እህት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “የመታሰቢያው በዓል ንግግር በቴሌቪዥን እንደሚሰራጭ ስሰማ ‘በኮቪድ-19 ምክንያት ያመለጠንን መጋበዣ ወረቀት የማሰራጨት ዘመቻ መልሰን አገኘነው’ ብዬ አሰብኩ። ወዲያውኑ ለጥናቶቼ፣ ለተመላልሶዎቼና ለማውቃቸው የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች በሙሉ ደውዬ ስለ ቴሌቪዥን ስርጭቱ ነገርኳቸው። ዘጠኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ንግግሩን ተመልክተዋል። አንዲት ዘመዴ ፕሮግራሙን በዚጉዊንቾር ቋንቋ በቴሌቪዥን ከተመለከተች በኋላ ስለ ጉዳዩ ይበልጥ መወያየት እንደምትፈልግ ነገረችኝ፤ እኔም በደስታ ተስማማሁ።”
ይህ ልዩ ዝግጅት በይሖዋ ዘንድ ‘ሁሉ ነገር እንደሚቻል’ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። —ማቴዎስ 19:26