በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወንድም ኦ ቤተሰብ አንድ ላይ የመታሰቢያውን በዓል ሲያከብሩ። አባትየው እና ሁለቱ ልጆች (በስተ ግራ) ቤት ሆነው የመታሰቢያውን በዓል አክብረዋል። ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተከታተለች ያለችው እናትየው (በስተ ቀኝ) ደግሞ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት አብራቸው በዓሉን እያከበረች ነው

ሚያዝያ 22, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የ2020 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—በእስያ

በጃፓን እና በደቡብ ኮሪያ የሚኖሩ አረጋውያንና ሕመምተኛ አስፋፊዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ፕሮግራሙን ተከታተሉ

የ2020 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—በእስያ

በሐኪም ቤቶችና በመጦሪያ ተቋማት የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች በኮቪድ-19 የተነሳ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። እነዚህ ወንድሞች ከተቋሙ መውጣት የማይችሉ ከመሆኑም ሌላ ጎብኚዎችም ወደ ውስጥ መግባት አይፈቀድላቸውም። እንዲህ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም በጉባኤ ሽማግሌዎች እርዳታ እነዚህ ወንድሞች በዓመት ውስጥ ልዩ ቦታ የሚሰጠውን በዓል ማክበር ችለዋል።

ደቡብ ኮሪያ

በናጁ ከተማ የሚኖሩት የ91 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እህት ኢ ጆም ሱን እና የ88 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እህት ግዎን ኤ ሱን ፍላጎት ካሳዩ የ96 ዓመት አረጋዊት ጋር ሆነው የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር። በመጦሪያ ተቋሙ ውስጥ ከሚሠሩት ሐኪሞች አንዱ የይሖዋ ምሥክር ነው። ይህ ወንድም የመታሰቢያውን በዓል ቤቱ ሆኖ ከጉባኤው ጋር ካከበረ በኋላ ወደ መጦሪያ ተቋሙ ተመለሰ። ከዚያም ለእነዚህ እህቶችና ፍላጎት ላሳዩት አረጋዊት የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም ከ​jw.org ላይ ከፈተላቸው። ወንድም ቂጣውንና የወይን ጠጁንም ጭምር አቅርቦላቸው ነበር።

በእይጆንግቡ ከተማ የሚኖረው ወንድም ቾይ ጄ ቾል የሚሠራው 14 አረጋውያን ወንድሞችና እህቶች በሚኖሩበት የመጦሪያ ተቋም ውስጥ ነው። ወንድማችን እነዚህ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በቪዲዮ ስርጭት አማካኝነት የመታሰቢያውን በዓል እንዲያከብሩ ዝግጅት አደረገ። በስብሰባው ላይ ከተገኙት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ጥናት ጀምረዋል።

የ59 ዓመቷ እህት ኪም ቴ ሱን የምትኖረው በቾናን ነው። እህት ኪም ከአምስት ዓመት በፊት ካንሰር እንዳለባት ታወቀ። ከተወሰነ ጊዜ በፊት ሕመሙ ስለጠናባት ሆስፒታል ገብታለች። ከእህት ኪም ቴ ሱን ጋር በአንድ የሆስፒታል ክፍል ውስጥ ሆና ሕክምናዋን የምትከታተል ኪም ጆንግ ሚ የተባለች ሌላ እህት አለች። ይህች እህት የ69 ዓመት ሴት ስትሆን እሷም የካንሰር ሕመምተኛ ነች። እነዚህ እህቶች በወረርሽኙ ምክንያት ከሆስፒታል መውጣት አይችሉም። ሆኖም ሁለቱም በጉባኤ ሽማግሌዎች እርዳታ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የመታሰቢያውን በዓል ከጉባኤያቸው ጋር ማክበር ችለዋል።

ሁለቱም እህቶች ደብዳቤ በመጻፍ ልባዊ ምስጋናቸውን ለሽማግሌዎች ገልጸዋል። በደብዳቤያቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የራሳችን የጤና ችግር ቢኖርም የመታሰቢያውን በዓል እንድናከብርና ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጥሩ ጊዜ እንድናሳልፍ ስለረዳችሁን በጣም እናመሰግናለን።”

ጃፓን

በሚዬ ግዛት፣ ጃፓን የሚኖሩት የ70 ዓመቷ እህት ሚኤኮ ፉጂዋራ ለሕክምና ሆስፒታል ገብተዋል። በሆስፒታሉ ውስጥ የዋይፋይ ኢንተርኔት ስለሌለ እህታችን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ከጉባኤያቸው ጋር የመታሰቢያውን በዓል ማክበር አልቻሉም። ሆኖም አንድ የጉባኤ ሽማግሌና ባለቤቱ ንግግሩን አስቀድመው ወደ ሞባይል ስልካቸው ልከውላቸው ስለነበር በሆስፒታል ክፍላቸው ሆነው ንግግሩን ማዳመጥ ችለዋል።

የ102 ዓመቷ እህት ዩኪ ቴክቺ የሚኖሩት በዛማ ከተማ፣ ካናጋዋ ግዛት በሚገኝ የመጦሪያ ተቋም ውስጥ ነው። የመታሰቢያው በዓል ከመድረሱ በፊት ልጃቸውና ባለቤቷ ቂጣውንና የወይን ጠጁን አሽገው ላኩላቸው። ከዚያም እህት ዩኪ ከልጃቸውና ከአማቻቸው ጋር በስልክ የመታሰቢያውን በዓል አክብረዋል።

አማቻቸው ወንድም ሚሙራ እንዲህ ብሏል፦ “የባለቤቴ እናት የተጠመቁት በ1954 ሲሆን አንዴም ቢሆን የመታሰቢያው በዓል አምልጧቸው አያውቅም። በዚህ ዓመት የመታሰቢያውን በዓል ያከበሩት ለየት ባለ መንገድ ቢሆንም በዓሉ ስላላመለጣቸው በጣም ተደስተዋል።”

እነዚህ አረጋውያንና ሕመምተኛ አስፋፊዎች በጉባኤ ሽማግሌዎቻቸው እገዛ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ያደረጉትን ጥረት ይሖዋ እንዳስተዋለ እርግጠኞች ነን።—ዕብራውያን 6:10