በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የበላይ አካል አባላት የመታሰቢያውን በዓል ንግግር ሲያቀርቡ፦ (በስተ ግራ) ወንድም አንቶኒ ሞሪስ ለቤቴል ቤተሰብ የተላለፈውን ንግግር ሲያቀርብ፤ (ከላይ በስተ ቀኝ) ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን እና (ከታች በስተ ቀኝ) ወንድም ማርክ ሳንደርሰን ክፍላቸው ሆነው በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ለጉባኤዎች ንግግር ሲያቀርቡ

ሚያዝያ 10, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የ2020 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—በዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል

የ2020 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—በዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል

ሚያዝያ 7, 2020 በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መሃል የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት መታሰቢያ አክብረዋል። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን ሌት እንደገለጸው “ይሖዋ እና ኢየሱስ ላደረጉልን ነገር ያለንን አድናቆት የሚቀንስ ወይም የጌታ ራትን ለማክበር ያለንን ቁርጠኝነት የሚያዳክም ምንም ዓይነት ቫይረስ ወይም ወረርሽኝ በዓለም ላይ ሊኖር አይችልም።” የዚህ ሐሳብ እውነተኝነት ዘንድሮ የታየው እንዴት ነው?

ይህ ርዕስ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞቻችን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መሃል የመታሰቢያውን በዓል ያከበሩት እንዴት እንደሆነ ከሚገልጹ ተከታታይ ዜናዎች መካከል የመጀመሪያው ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ የመታሰቢያው በዓል በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤትና በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ የተከበረው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

መንግሥት ከስብሰባዎች ጋር በተያያዘ ያወጣውን ሕግ ለማክበር ሲባል የበላይ አካሉ የመታሰቢያው በዓል ንግግር ለሁሉም የቤቴል ቤተሰብ አባላት እንዲተላለፍ ወሰነ። ንግግሩ የቀረበው ዎርዊክ በሚገኘው አዳራሽ ውስጥ ሲሆን ንግግሩን ያቀረበው ወንድም አንቶኒ ሞሪስ ነው። ሁሉም የዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል ቤተሰብ አባላት ከክፍላቸው ሆነው ፕሮግራሙን መከታተል ይችሉ ነበር። ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት ጥቂት ቤቴላውያን ብቻ ቢሆኑም የቤቴል ቢሮ ሁሉም ቤቴላውያን ቂጣና የወይን ጠጅ እንዲያገኙ ዝግጅት አድርጓል።

የቤቴል ቤተሰብ አባላት ለበዓሉ የሚጠቀሙበት ቂጣና የወይን ጠጅ ተደርድሮ

ከዚህም ሌላ ቤቴላውያን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ከጉባኤያቸው ጋር በዓሉን የማክበር አማራጭ ነበራቸው። በተጨማሪም የጉባኤ ሽማግሌ የሆኑ ቤቴላውያን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት የመታሰቢያውን በዓል ንግግር የማቅረብ አማራጭ ተሰጥቷቸው ነበር።

በዎልኪል ቤቴል የሚያገለግሉ ባልና ሚስት ክፍላቸው ውስጥ ሆነው የመታሰቢያውን በዓል ሲያከብሩ

የዘንድሮ የመታሰቢያው በዓል እስከ ዛሬ ከተከበሩት ሁሉ እጅግ ልዩ እንደነበር በርካታ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ገልጸዋል። ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር በአካል ቢራራቁም በዓለም ዙሪያ ካሉ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር አንድ እንደሆኑ ተሰምቷቸዋል፤ ምክንያቱም በዚህ ወቅት ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳዩትን ታላቅ ፍቅር እያሰቡ ነበር።—ዮሐንስ 3:16፤ ማቴዎስ 20:28