በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 3, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የ2020 የአምላክን መንግሥት የማሳወቅ ዘመቻ፦ የመንግሥት ባለሥልጣናት የላኩት የአድናቆት መልእክት

የ2020 የአምላክን መንግሥት የማሳወቅ ዘመቻ፦ የመንግሥት ባለሥልጣናት የላኩት የአድናቆት መልእክት

በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የኅዳርን ወር ያሳለፉት፣ ቁጥር 2 2020 መጠበቂያ ግንብን (ለሕዝብ የሚበረከተው እትም) በማሰራጨት ነው፤ ይህን መጽሔት በንግድ ቦታዎች፣ ለቤተሰባቸው አባላትና ፍላጎት ላላቸው ሌሎች ሰዎች አሰራጭተዋል። የዚህ ዘመቻ ለየት ያለው ገጽታ፣ መጽሔቱ በሁሉም እርከን ላይ ለሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት መሰራጨቱ ነው። በምላሹም ቅርንጫፍ ቢሮዎች የአድናቆት መልእክቶች እየጎረፉላቸው ነው።

የሴራ ሊዮን የመሬትና የቤቶች ልማት ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር የሆኑት ሬክስ ቦናፋ፣ ወንድሞች መጽሔቱን ስለላኩላቸው የምስጋና ደብዳቤ ጽፈዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “የላካችሁልኝ መጽሔት በጣም አበረታችና አስተማሪ እንደሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ፤ አሁን በየቀኑ ከማነባቸው ጽሑፎች አንዱ ሆኗል።”

የሳሞአ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የጌታ ጸሎት ያለውን ጠቀሜታ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ በመግለጽ የምስጋና ደብዳቤ ልከዋል። የሳሞአ ፕሬዚዳንት የሆኑት ትዊማሊያሊፋኖ ቫሌቶዋ ሱላዉቪ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር የምናከናውነውን ሥራ እንደሚያደንቁ ገልጸዋል። ይህ ሥራ “ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተምረው ሕይወታቸውን እንዲለውጡ በማድረግ ማኅበረሰቡን እየጠቀመ እንዳለ” ተናግረዋል። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአካል መገናኘትን የሚጠይቁ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን እንዲሁም ከቤት ወደ ቤት የሚያደርጉትን አገልግሎት ለጊዜው ማቆማቸው እንደሚያስመሰግናቸው እኚህ ሰው ገልጸዋል።

ኦስቫልዶ ካርታጌና ጋርሲያ የተባሉ አንድ የቺሊ የመንግሥት ባለ ሥልጣን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የተከበረ ዓላማ ያለው ይህ የምታደርጉት ዘመቻ በመላው አገሪቱ ያሉ ባለሥልጣናትን ግንዛቤ እንደሚያሰፋ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በተለይ ደግሞ አሁን አገራችንንም ሆነ ዓለማችንን ከገጠመው ቀውስ አንጻር ችግሩን በማቃለል ለመላው ማኅበረሰብ ጥሩ ሥራ እንዲሠሩ ያነሳሳቸዋል ብዬ እጠብቃለሁ።”

የጀርመን ፓርላማ አባል የሆኑ አንድ ሰው፣ ጀርመን ውስጥ ለሚገኘው የማዕከላዊ አውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ሃይማኖታችሁን በደንብ አውቀዋለሁ። የሃይማኖታችሁ አባላት የይሖዋ ምሥክር እንደሆኑ በድፍረት በመናገር የሚያሳዩትን አቋም አከብራለሁ። . . . በተጨማሪም የሃይማኖታችሁ አባላት በሦስተኛው ራይክ (በናዚ አገዛዝ) ዘመን እጅግ ከባድ ስደት እንደደረሰባቸው አውቃለሁ።”

በተመሳሳይም አንድ የጀርመን ፌደራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን ለማጽናናት ለሚያደርጉት ጥረት ያለውን አድናቆት ገልጿል። “የምታከናውኑት ሥራ፣ ማኅበረሰባችን አንድነት እንዲኖረው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው” ብሏል።

በኮሎምቢያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልና የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑ ሁለት ባለሥልጣናት ለተላከላቸው መጽሔት ምስጋናቸውን ለመግለጽ ለቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ጽፈዋል፤ መጽሔቱን ለሌሎች እንደሚያጋሩም ገልጸዋል። በአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥ የሚሠሩ አንድ ባለሥልጣን ደግሞ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ይህን መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ስለላካችሁልኝ በጣም አመሰግናለሁ፤ መጽሔቱ የያዘው መልእክት ሕይወት አድን ነው!”

ጃፓን ውስጥ የጋና አምባሳደር ሆነው የሚያገለግሉት ፍራንክ አኬሪ እንዲህ ብለዋል፦ “መጽሔቱን ትልቅ ቁም ነገር አግኝቼበታለሁ፤ የሰው ዘር ላጋጠሙት ብዙ ችግሮች መፍትሔው ምን እንደሆነ ጎላ አድርጎ ይገልጻል።”

በተመሳሳይም የአዘርባጃን አምባሳደር እንዲህ ብለዋል፦ “ይህን ልዩ የመጠበቂያ ግንብ እትም ለኤምባሲያችን ስለላካችሁልን በጣም አመሰግናችኋለሁ። መጽሔቱን ያነበብኩት በከፍተኛ ጉጉት ነው።”

የሞዛምቢክ ቅርንጫፍ ቢሮ የመረጃ ዴስክ የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም አማሮ ቴሼራ በተናገረው ሐሳብ ሁላችንም እንስማማለን፤ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ዘመቻ እስካሁን እንኳ ካሰብነው የበለጠ ውጤት አስገኝቷል። ብዙውን ጊዜ በቀላሉ የማይገኙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት መስማት ችለዋል።”

የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ‘በሥልጣን ላይ ላሉ’ እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች ለማድረስ የምናደርገው ጥረት እየቀጠለ ሲሄድ ተጨማሪ የአድናቆት መልእክቶች እንደሚደርሱን ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ጢሞቴዎስ 2:2