ነሐሴ 31, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የ2020 የአገልግሎት ዓመት ጎላ ያሉ ዜናዎች
በ2020 የአገልግሎት ዓመት በመላው ዓለም ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በመንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ለየት ያለ ፈተና አጋጥሟቸዋል። ሆኖም ያጋጠማቸው ፈተና ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ታማኝነታቸውንና አንድነታቸውን ለመጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይቷል።
ዋነኛው ፈተና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ነበር፤ ይህ ወረርሽኝ ለረጅም ዘመናት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በዓለም ዙሪያ ብዙ ትርምስ ፈጥሯል።
የይሖዋ ምሥክሮች ለወረርሽኙ ፈጣን ምላሽ ሰጥተዋል። ለአምልኮ ለመሰብሰብ፣ እርስ በርስ ለመበረታታትና ምሥራቹን ለመስበክ አዳዲስ ዘዴዎችን አግኝተዋል።
በዚህ አስደናቂ ዓመት የታዩ አንዳንድ ‘መልካም ዜናዎችን’ እንመልከት።—ምሳሌ 15:30
አዳዲስ መጽሐፍ ቅዱሶች
በዚህ የአገልግሎት ዓመት ድርጅታችን አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ ወይም በከፊል በ36 ቋንቋዎች አውጥቷል። ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተጣሉ ገደቦች የተነሳ አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሶች የወጡት በቪዲዮ በተደረጉ ስብሰባዎች ላይ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት ነበር። በአሁኑ ወቅት አዲስ ዓለም ትርጉም በሙሉ ወይም በከፊል በ193 ቋንቋዎች ይገኛል።
የበላይ አካሉ ሪፖርቶች
ከመጋቢት 18, 2020 አንስቶ የበላይ አካል አባላት ከወረርሽኙ ጋር የተያያዙ ልዩ ወርሃዊ ፕሮግራሞችን በjw.org እና በJW Library ላይ ሲያወጡ ቆይተዋል።
በመጀመሪያው ሪፖርት ላይ ወንድም ስቲቨን ሌት ወረርሽኙ አስጨናቂ ሁኔታ ቢፈጥርም “የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት መጨረሻ ላይ እንደሆነ ከምንጊዜውም ይበልጥ ግልጽ” እንደሚያደርግልን ተናግሯል። “የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት መጨረሻ፣ መጨረሻ ላይ ነው!” ብሏል።
ወንድም ሌት “ሁኔታው ከባድ እንደሆነ ባይካድም የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ልንሸበር አይገባም” በማለት ተናግሯል።
ሁሉም የበላይ አካሉ ሪፖርቶች ከተለያዩ አገሮች የተገኙ አበረታች ሪፖርቶችን ይዘዋል። እነዚህ ሪፖርቶች የበላይ አካሉን አመራር መቀበል የሚያስገኘውን ጥቅም ያሳያሉ። በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት የወንድማማች ማኅበራችን ለወረርሽኙ ፈጣንና ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምላሽ በመስጠቱ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በዓይነቱ ልዩ የሆነ የመታሰቢያው በዓል
ላለፉት በርካታ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ የጌታ ራትን ለማክበር ሲሰበሰቡ ቆይተዋል። ዘንድሮ ግን አንድ ላይ መሰብሰብ በብዙ አገሮች የማይመከር ወይም የማይፈቀድ ነገር ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ግለሰቦችና ቤተሰቦች የራሳቸውን ቂጣና የወይን ጠጅ በማቅረብ የመታሰቢያውን በዓል ንግግር በቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ አማካኝነት ተከታትለዋል።
ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች የመታሰቢያውን በዓል በቪዲዮ ኮንፈረንሲንግ አማካኝነት ማካሄድ አልተቻለም። አፍሪካ ውስጥ ያሉ 11 ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። እነዚህ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የመታሰቢያው በዓል ንግግር በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ጣቢያዎች እንዲሰራጭ ዝግጅት አደረጉ። ይህ ዝግጅት ከ407,000 የሚበልጡ አስፋፊዎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ፕሮግራሙን እንዲከታተሉ መንገድ ከፍቷል።
በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ጣቢያዎች አማካኝነት ስብሰባ ማሰራጨት
የበላይ አካሉ በመታሰቢያው በዓል ወቅት ጥቅም ላይ የዋለውን ዘዴ በመጠቀም አንዳንድ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የጉባኤ ስብሰባዎችን እንዲያሰራጩ ፈቃድ ሰጠ። በዚህ መንገድ በድሃ አገሮች ውስጥ ያሉ አስፋፊዎች በሬዲዮና በቴሌቪዥን አማካኝነት የጉባኤ ስብሰባዎችን መከታተል ችለዋል። እስካሁን ድረስ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ 23 ቅርንጫፍ ቢሮዎች በዚህ ዝግጅት ተጠቅመዋል።
የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ተፈታታኝ ሆኖባቸዋል። በዓለም ዙሪያ ከ400 የሚበልጡ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል፤ ጉባኤው አስፋፊዎች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ መርዳት ካልቻለ እነዚህ ኮሚቴዎች እርዳታ ያበረክታሉ። በ2020 የአገልግሎት ዓመት የበላይ አካሉ በኮቪድ-19 ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ከ330,000 የሚበልጡ አስፋፊዎችን ለመርዳት ከ18 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ መድቧል።
በቪዲዮ የተካሄዱ የክልል ስብሰባዎች
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የክልል ስብሰባው በቪዲዮ አማካኝነት ተካሂዷል። የበላይ አካል አባላትና ረዳቶቻቸው ሁሉንም የክልል ስብሰባ ንግግሮች ሲያቀርቡ ተቀረጹ። ከዚያም ቪዲዮዎቹ ከ500 ወደሚበልጡ ቋንቋዎች ተተረጎሙ። የክልል ስብሰባው jw.org እና JW Library ላይ የወጣ ሲሆን አስፋፊዎችና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ቤታቸው ሆነው ደህንነታቸውን በጠበቀ መልኩ ፕሮግራሙን መከታተል ችለዋል።
በወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰው ስደት ቀጥሏል
በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከወረርሽኙ በተጨማሪ ከባድ ስደትን መቋቋም አስፈልጓቸዋል።
ሩሲያ ውስጥ ባለፈው ዓመት በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ቤታቸው ተበርብሯል እንዲሁም ለእስር ተዳርገዋል። በአሁኑ ወቅት ሩሲያ ውስጥ 42፣ ክራይሚያ ውስጥ ደግሞ 2 ወንድሞችና እህቶች ታስረዋል። የሩሲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2017 ፍርድ ካስተላለፈበት ጊዜ አንስቶ ከ1,000 የሚበልጡ ወንድሞቻችን ቤታቸው ተበርብሯል።
ብዙ ወንድሞቻችን የታሰሩት ኤርትራ ውስጥ ነው፤ በአሁኑ ወቅት 52 ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በእስር ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል በሕሊናቸው የተነሳ የውትድርና አገልግሎት ባለመስጠታቸው ምክንያት ከመስከረም 17, 1994 አንስቶ የታሰሩት ጳውሎስ እያሱ፣ ይስሃቅ ሞገስ እና ነገደ ተኽለማርያም ይገኙበታል። ተጨማሪ 26 ወንድሞችና እህቶች ደግሞ ከአሥር ዓመት በላይ ታስረዋል።
በእስር ላይ ያሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሙሉ ደፋሮች እንዲሆኑ መጸለያችንን እንቀጥላለን። ፈተናን በጽናት በመቋቋም ታማኝነታቸውን እያስመሠከሩ እንዳሉ እንተማመናለን።—ራእይ 2:10
በታማኝነት ጸንተዋል
ባለፈው የአገልግሎት ዓመት በመላው ዓለም ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት አስመሥክረዋል፤ ይህን ያደረጉት አማራጭ የስብከት ዘዴዎችን በመጠቀም፣ እርስ በርስ ለመበረታታት አዳዲስ መንገዶችን በመፈለግ እንዲሁም የበላይ አካሉና የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚሰጡትን መመሪያ በጥንቃቄ በመታዘዝ ነው።
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለአምላክ ያደሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ የተለያዩ ተግባሮችን በመፈጸም ለፈጣሪ ያላቸውን ፍቅር አሳይተዋል። በተጨማሪም ወደፊት የሚጠብቋቸውን ከባድ ፈተናዎች በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል መሠረት ጥለዋል።—ያዕቆብ 1:2, 3