መስከረም 3, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የ2020 የክልል ስብሰባ—በመላው ዓለም በቪዲዮ የተላለፈ የመጀመሪያው ስብሰባ
በሐምሌ እና በነሐሴ 2020 በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የ2020ን የክልል ስብሰባ በአንድነት ተከታትለዋል።
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ‘ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ’! የተባለው የክልል ስብሰባ በ240 አገሮች በሚገኙ የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች፣ ስታዲየሞችና ሌሎች የመሰብሰቢያ ቦታዎች ሊካሄድ ታቅዶ ነበር። ሆኖም የበላይ አካሉ የተሰብሳቢዎቹን ጤንነት ለመጠበቅ ሲል የክልል ስብሰባው በመላው ዓለም በቪዲዮ እንዲተላለፍ ወሰነ። ከ1897 ወዲህ ድርጅቱ፣ ተሰብሳቢዎች በአካል ያልተገኙበት ስብሰባ ሲያካሂድ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው።
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ኬነዝ ኩክ እንዲህ ብሏል፦ “የክልል ስብሰባዎቹ ሲሰረዙ ግባችን ሁሉም ሰው በተመሳሳይ ጊዜ የሚከታተለው ዓለም አቀፋዊ ፕሮግራም ማዘጋጀት ነበር። ፕሮግራሙን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ለማዘጋጀት ያለን ጊዜ ከአራት ወር ያነሰ እንደሆነ ተገንዝበን ነበር። በአብዛኛው እንዲህ ያለውን ፕሮግራም ለማቀድና ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ወይም ከዚያ የሚበልጥ ጊዜ ይፈጃል። የክልል ስብሰባው የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ ሐምሌ 6, 2020 ወደ 400 በሚጠጉ ቋንቋዎች መውጣቱን ስናይ በጣም ተደሰትን። ፕሮግራሙ በ511 ቋንቋዎች እንደሚወጣ እንጠብቃለን!”
ሦስት ልጆቿን ብቻዋን የምታሳድግ አንዲት እህታችን የክልል ስብሰባው በዚህ መልክ መተላለፉ ያስገኘውን ጥቅም ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ከወንድሞችና እህቶች ጋር አብረን መሰብሰብ አለመቻላችን ቢያሳዝነንም ፕሮግራሙ በዚህ መንገድ መቅረቡ ለልጆቼ በጣም ጠቅሟቸዋል። ስብሰባው ተከፋፍሎ መቅረቡ ትኩረታቸው ሳይከፋፈል ለመከታተል በጣም ረድቷቸዋል። በመሃል አረፍ ማለት ከፈለጉ ቪዲዮውን ማቆም እንችላለን። ምንም ነገር አያመልጠንም። የዓርብ ዕለት ፕሮግራም ልጆች እንደ ፍላጻ እንደሆኑና ወላጆች፣ ልጆቻቸው ይሖዋን ማገልገል የሚያስገኘውን አስደሳችና አርኪ ሕይወት እንዲያጣጥሙ ለመርዳት ፍላጻዎቹን በጥንቃቄ ማነጣጠር እንዳለባቸው የሚያጎላ ነበር። የክልል ስብሰባው በቪዲዮ አማካኝነት መቅረቡ ይህን ለማድረግ እየረዳኝ ነው።”—መዝሙር 127:4
ይህ ታሪካዊ የክልል ስብሰባ የዓለም አቀፉን ሚዲያ ትኩረት ስቧል። ለምሳሌ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዴስክ አስተባባሪ የሆነው ወንድም ሮበርት ሄንድሪክስ እንዲህ ብሏል፦ “በርካታ ጋዜጠኞች በቪዲዮ ስለቀረበው የክልል ስብሰባ ዘግበዋል። ድርጅታችን ደህንነትን አደጋ ላይ በማይጥል መንገድ የክልል ስብሰባውን ለማከናወን ቴክኖሎጂን የተጠቀመው እንዴት እንደሆነ በዘገባቸው ላይ ገልጸዋል።”
‘ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ’! የተባለው የ2020 የክልል ስብሰባ ይሖዋ ታላቅ አስተማሪያችን መሆኑን አዲስና አስገራሚ በሆነ መንገድ አረጋግጦልናል።—ኢሳይያስ 30:20