በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ቬኔዙዌላ፦ አንዲት እህት በዋራዎ ቋንቋ ስትቀዳ (ከላይ በስተ ግራ)፣ በፒያሮአ ትርጉም ቡድን ውስጥ የሚያገለግሉ ሁለት ወንድሞች በሥራ ላይ (ከታች በስተ ግራ)። ደቡብ ኮሪያ፦ አንድ ቤተሰብ የ2020⁠ን የክልል ስብሰባ ሲመለከት (በስተ ቀኝ)

መስከረም 4, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የ2020 የክልል ስብሰባ—ተርጓሚዎች እንቅፋቶችን አሸነፉ

የ2020 የክልል ስብሰባ—ተርጓሚዎች እንቅፋቶችን አሸነፉ

“ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ”! የተባለው የ2020 የክልል ስብሰባ በይሖዋ ምሥክሮች ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ክንውን ነበር። ስብሰባው ከ500 ወደሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በቪዲዮ ተሰራጭቷል። ተርጓሚዎች የቁሳቁስና የጊዜ እጥረት ቢኖርባቸውም እንቅፋቶቹን አሸንፈዋል።

በኬንያ የሚገኘው የኪኩዩ ትርጉም ቡድን አባል የሆነች አንዲት ተርጓሚ እንዲህ ብላለች፦ “በቅርንጫፍ ቢሮው የእንቅስቃሴ ገደብ ስለተጣለ መቅዳት የምንችለው ጥቂት ሰዎችን ብቻ ነበር። ይህን ችግር ለመፍታት በሌሎች ቦታዎች ያሉ ወንድሞችና እህቶችን ተጠቀምን። የይሖዋ መንፈስ ያከናወነውን ነገር ማየታችን በጣም አስደስቶናል።”

የኮሪያ ምልክት ቋንቋ ትርጉም ቡድንና የኮሪያኛ ትርጉም ቡድን ተመሳሳይ እንቅፋት አጋጥሟቸው ነበር። ቡድኑን የሚያግዙ የርቀት ፈቃደኛ ሠራተኞች ለቅጂ ወደ ቤቴል መምጣት አልቻሉም።

አንድ ወንድም በኮሪያ ምልክት ቋንቋ ንግግሮችንና ቪዲዮዎችን ለመቅረጽ በቤቱ ያዘጋጀው ጊዜያዊ ስቱዲዮ

ይህን እንቅፋት ለማሸነፍ ወንድሞች በየቤታቸው ስቱዲዮ አዘጋጁ። አብዛኛው የቀረጻ ቁሳቁስ የተገኘው የአካባቢው ወንድሞች ባደረጉት ልግስና ነበር። በተጨማሪም ሁሉም ትላልቅ ስብሰባዎች ስለተሰረዙ ቅርንጫፍ ቢሮው በትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ከነበሩት ካሜራዎች መካከል የተወሰኑትን የምልክት ቋንቋ ቪዲዮዎችን ለመቅረጽ ተጠቅሞባቸዋል።

በቬኔዙዌላ አንዳንድ ተርጓሚዎች የኢንተርኔት ችግር እንቅፋት ሆኖባቸው ነበር። ሌሎቹ ደግሞ የቁሳቁስ እጥረት አጋጥሟቸዋል። ሆኖም እነዚህ ተርጓሚዎች ዘዴኛ በመሆናቸው በእጃቸው ያለውን ቁሳቁስ ተጠቅመው ሥራቸውን አከናውነዋል። ለምሳሌ በአንድ አካባቢ ያሉ ተርጓሚዎች ቅጂ ሲያከናውኑ ከውጭ ድምፅ እንዳይገባ ለመከላከል ፍራሽ ተጠቅመዋል።

በጁባ፣ ደቡብ ሱዳን ወደ ዛንዴ ቋንቋ የሚተረጉም አንድ የትርጉም ቡድን አለ። ከተርጓሚዎቹ መካከል አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “ሙሉውን የክልል ስብሰባ መቅዳት እንዳለብን ሳውቅ ‘ይሄማ ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም! ከ90 የሚበልጡ ቪዲዮዎች ያሉትን ፕሮግራም በሁለት ወር ውስጥ መቅዳት አንችልም’ ብዬ አስቤ ነበር። ፕሮጀክቱ መሳካቱን ሳይ ግን ይሖዋ ዓላማውን እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ሙሉ በሙሉ ተማመንኩ። ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድ በጣም አስደናቂ ነው!”—ማቴዎስ 19:26

በእርግጥም “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ”! የተባለው የ2020 የክልል ስብሰባ ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ነው፤ “የእሱ ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 2:4