በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም አሌክሳንደር ኡርሱ

ታኅሣሥ 4, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና

የ80 ዓመቱ ወንድም አሌክሳንደር ኡርሱ በጽናት ያሳለፈውን ሕይወት ሲተርክ

የ80 ዓመቱ ወንድም አሌክሳንደር ኡርሱ በጽናት ያሳለፈውን ሕይወት ሲተርክ

“ይሖዋ ያን ጊዜ ተንከባክቦናል፤ ወደፊትም መንከባከቡን እንደሚቀጥል አውቃለሁ።”

ወቅቱ ኅዳር 15, 2018 አመሻሹ ላይ ነው። በጃንኮይ፣ ክራይሚያ የሚኖረው የ78 ዓመቱ ወንድም አሌክሳንደር ኡርሱ ልጁን ቪክቶርን ለመቀበል ከቤቱ ወጣ አለ። ድንገት በዋናው በር በኩል ኃይለኛ መብራት በራበት። ቀስ እያለ ወደ ብርሃኑ አቅጣጫ አመራ። በዚህ ጊዜ፣ አንድ ፖሊስ “ቁም! እንዳትነቃነቅ!” ብሎ ሲጮኽ ሰማ።

መጀመሪያ ላይ አሌክሳንደር፣ ወንድሞች ለቀልድ ያደረጉት መስሎት ነበር፤ ወዲያውኑ ግን ጉዳዩ ቀልድ እንዳልሆነ ገባው። ጭምብል ያጠለቀ አንድ ሰው እጆቹን በኃይል ጠምዝዞ ከኋላው ያዘው። ጭምብል ያጠለቀ ሌላ ሰው ደግሞ መንገጭላውን በቡጢ መታው። ከባድ መሣሪያ የታጠቁ ስድስት የፌዴራል ደህንነት አባላት አሌክሳንደርን እና ቪክቶርን ፈተሿቸው፤ በኋላም ቤቱን በርግደው ገቡ።

የደህንነት ሰዎቹ በሩን በርግደው ሲገቡ የአሌክሳንደር ሚስት ኒና ኩሽና ውስጥ ነበረች። አንደኛው የደህንነት አባል፣ ሞባይሏን ነጠቃትና ምን እየተመለከተች እንደሆነ ጠየቃት። የደህንነት ሰዎቹ ቤቱን ለሰዓታት በረበሩ፤ ሆኖም የሩሲያ መንግሥት ጽንፈኛ ብሎ የፈረጃቸውን ጽሑፎች ማግኘት አልቻሉም።

ወንድም አሌክሳንደር ኡርሱ ከባለቤቱ ከኒና ጋር በ2020

ውዱ ወንድማችን አሌክሳንደር አልታሰረም። ይሁንና አሌክሳንደርም ሆነ በሩሲያና በክራይሚያ ያሉ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች፣ ፖሊሶች በማንኛውም ሰዓት መጥተው ቤታቸውን ሊበረብሩና ሊያስሯቸው እንደሚችሉ ያውቃሉ። እንዲህ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመቋቋም አሌክሳንደር ማሰላሰልን ጠቃሚ ሆኖ አግኝቶታል፤ የቤተሰቡ አባላት ስለተዉት መልካም ምሳሌ እንዲሁም በሶቪየት አገዛዝ ወቅት እሱ ራሱ በስደት ስላሳለፈው ጊዜ ያሰላስላል።

ሐምሌ 6, 1949 አሌክሳንደር የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለ፣ የሶቪየት ወታደሮች በሌሊት ቤታቸውን ሰብረው ገቡ፤ ከዚያም ቤቱን በረበሩት። የቤቱን ዕቃዎች ሁሉ እያነሱ ወለሉ ላይ ከጣሉ በኋላ ጓዛቸውን እንዲሸክፉ አዘዟቸው። አሌክሳንደር እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “እናቴ ወታደሮቹ ሳያዩአት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ጓዛችን ውስጥ ደበቀች፤ ከእነዚህ ጽሑፎች አንዱ የአምላክ በገና የተባለው መጽሐፍ ነው።” ወታደሮቹ መላውን ቤተሰብ ይዘው ወደ ባቡር ጣቢያ ሄዱ።

ደፋር የሆኑት የአሌክሳንደር ቤተሰብም ሆነ ሌሎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ አዲሱ መኖሪያቸው ወደ ሳይቤሪያ የተጓዙት የመንግሥቱን መዝሙሮች እየዘመሩ ነበር። ከእነዚህ ወንድሞች በተጨማሪ ከ1949 እስከ 1951 ባሉት ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች ወደ ሳይቤሪያ ተግዘዋል።

በ1950ዎቹ ሳይቤሪያ ውስጥ የነበሩት ወንድሞች በእርሻ ቦታዎች ላይ በድብቅ ስብሰባ ያካሂዱ ነበር። አንዳንድ ቤተሰቦች በስብሰባዎቹ ላይ ለመገኘት 20 ኪሎ ሜትር ያህል በእግራቸው ይጓዙ ነበር።

አሌክሳንደር የቤተሰቡ አባላት ከተዉት ግሩም የእምነት ምሳሌ ተጠቅሟል። ቅድመ አያቱ ማካር፣ አያቱ ማክሲም፣ አጎቱ ቭላዲሚር እና አባቱ ፕዮትር ፈተናን በጽናት የተቋቋሙ የእምነት ሰዎች ነበሩ።

በስተ ግራ ያለው ፎቶግራፍ፣ ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድም አሌክሳንደር ኡርሱ ልጁን ቪክቶርን ይዞ፣ ባለቤቱ ኒና፣ እናቱ ናዴዥዳ፣ አባቱ ፕዮትር ዲናን (የአሌክሳንደርን ሴት ልጅ) ይዞ። በስተ ቀኝ ያለው ፎቶግራፍ፦ ወንድም ቭላዲሚር ኡርሱ (የአሌክሳንደር አያት የሆነው የማክሲም ወንድም ነው)። ቭላዲሚርም ሆነ ማክሲም እስር ቤት እያሉ በታማኝነት በሞት አንቀላፍተዋል

የአሌክሳንደር አባት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ በ1944 በአሥር ዓመት እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበት ነበር። ሦስት ዓመት ከታሰረ በኋላ ጀርባው ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት መንቀሳቀስ ስላቃተው ወደ ቤቱ እንዲመለስ ተደረገ። አሌክሳንደር፣ አባቱ ስለ ዳዊት፣ ስለ ጎልያድ እንዲሁም ዳዊትና ዮናታን ስለነበራቸው ጓደኝነት የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ይናገር እንደነበር ያስታውሳል።

አሌክሳንደር ስለ አጎቱ ስለ ቭላዲሚር ሲተርክ እንዲህ ብሏል፦ “አጎቴ ቭላዲሚር፣ ደብልዩ ቢ ቢ አር የሬዲዮ ጣቢያን አዘውትሮ ይከታተል እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ይደርሱት ነበር። ያን ጊዜ ሬዲዮ ይዞ መገኘት ሕገወጥ ነበር፤ ስለዚህ አጎቴ ምድር ቤት ውስጥ አንዲት አነስተኛ ክፍል አዘጋጀ፤ እሱም ሆነ ፍላጎት ያላቸው ሌሎች ሰዎች ከደብልዩ ቢ ቢ አር የሬዲዮ ጣቢያ የሚተላለፉትን ፕሮግራሞች እዚህች ክፍል ውስጥ ተደብቀው ያዳምጡ ነበር።”

በ1940ዎቹ ዓመታት፣ ፍላጎት አለኝ ብሎ የቀረባቸው አንድ ሰው ተደብቀው ሬዲዮ የሚያዳምጡበት ክፍል የሚገኝበትን ቦታ አጋለጠ። የአሌክሳንደር አጎትና አያት ተይዘው ታሰሩ፤ የታሰሩት በምዕራባዊ ዩክሬን፣ ከመኖሪያ መንደራቸው 80 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው በሆቲን ነበር።

አሌክሳንደር እንዲህ ብሏል፦ “ሴት አያቴ ልትጠይቃቸው ወደ እስር ቤት ትሄድ ነበር። እምነታቸው ደስተኛ እንዲሆኑ እንደረዳቸው ሆኖም ድብደባ ሳይደርስባቸው እንደማይቀር ስትነግረን ትዝ ይለኛል።” የሚያሳዝነው፣ የአሌክሳንደር አጎትና አያት እዚያው እስር ቤት ሳሉ ሕይወታቸው አልፏል።

“እስር ቤት ሳሉ ምን እንዳጋጠማቸው፣ ምን እንዳደረጓቸው፣ እንዴት እንደሞቱና የት እንደተቀበሩ አሁንም የምናውቀው ነገር የለም” በማለት አሌክሳንደር ተናግሯል። አክሎም “ሆኖም እስከ ሞት ድረስ ለይሖዋ ታማኝ እንደሆኑ ማወቃችን አበረታቶናል” ብሏል።

አሌክሳንደር፣ የቤተሰቡ አባላት የተዉት ግሩም ምሳሌና እሱ ራሱ በሳይቤሪያ ያጋጠመው ነገር አሁን ለሚደርስባቸው ስደት አዘጋጅቶታል። “ከልጅነቴ ጀምሮ እያየሁ ያደግኩት ነገር ስለሆነ የቤቴ መበርበር አላስደነቀኝም። ይሖዋ ያን ጊዜ ተንከባክቦናል፤ ወደፊትም መንከባከቡን እንደሚቀጥል አውቃለሁ” ብሏል።

“ጸንቼ እንድቆም የረዳኝ ሌላው ነገር በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴና ማሰላሰሌ፣ አዘውትሬ ስብሰባ ላይ መገኘቴ እንዲሁም ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር መቀራረቤ ነው” በማለት ተናግሯል።

አሌክሳንደር ፍርድ ቤት ስለቀረቡ ወንድሞች የሚገልጹ ዘገባዎችንም አዘውትሮ ያነባል፤ የእነሱ የድፍረት ምሳሌ ብርታት ሰጥቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ወንድሞች ለፍርድ ቤቱ የተናገሩትን የመጨረሻ ሐሳብ አነባለሁ። በድፍረት የሚሰጡት ምሥክርነት ኢየሱስ ‘በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ በዚያ ጊዜ ለእነሱም ሆነ ለአሕዛብ መመሥከር ትችላላችሁ’ በማለት የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል።”—ማቴዎስ 10:18

ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስደትን መቻል ብቻ ሳይሆን በደስታ መወጣት ችለዋል፤ ይህን ማድረግ የቻሉት አምላካችን ይሖዋ በፍቅር በሚያደርግላቸው ድጋፍ ነው። እነዚህ ወንድሞች፣ ዳዊት የተናገረውን ሐሳብ እውነተኝነት የሚያረጋግጡ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው፤ ዳዊት በመንፈስ መሪነት “[ይሖዋን] መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ግን ሐሴት ያደርጋሉ፤ ምንጊዜም በደስታ እልል ይላሉ” ብሏል።—መዝሙር 5:11