መጋቢት 10, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ወጡ
መጋቢት 5, 2023 በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ በተካሄደ ልዩ ፕሮግራም ላይ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን፣ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መውጣታቸውን አብስሯል፤ እነሱም በደቡብ አፍሪካ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጀው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም እና በእንዶንጋ ቋንቋ የተዘጋጀው የማቴዎስ መጽሐፍ ትርጉም ናቸው። ብዙ ጉባኤዎች ፕሮግራሙን በያሉበት ሆነው በቀጥታ ተከታትለዋል። አጠቃላይ ፕሮግራሙን የተከታተሉት ሰዎች ቁጥር ከ130,000 በላይ ነው። እነዚህ ትርጉሞች መውጣታቸው እንደተነገረ ኤሌክትሮኒክ ቅጂዎች ተለቅቀዋል።
በደቡብ አፍሪካ የምልክት ቋንቋ የትርጉም ሥራ የጀመረው በ2007 ነው፤ ሥራው የሚካሄደው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ጆሃንስበርግ አቅራቢያ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ነበር። በ2022 የትርጉም ቡድኑ ደርባን ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ የርቀት የትርጉም ቢሮ ተዛወረ። አያንዳ ምዳቤ የተባለ መስማት የተሳነው ወንድም፣ አሁን የወጣውን የምልክት ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ትርጉም፣ የአምላክ ቃል ያለው ኃይልና እውነተኝነቱ ይበልጥ ውስጣችን ጠልቆ እንዲገባ አድርጓል። በደቡብ አፍሪካ ምልክት ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ በመመልከት ስለ ኢየሱስ ባሕርያት እንዲሁም በጥቅሉ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች የተሻለ ግንዛቤ እያገኘሁ ነው። ይህም አስተሳሰቤን ጥሩ አድርጎ እየቀረጸው ነው።”
እንዶንጋ በዋነኝነት ናሚቢያ ውስጥ የሚነገር ቋንቋ ነው፤ የርቀት የትርጉም ቢሮው የሚገኘውም ኦንዳንግዋ ውስጥ ነው። a ከተርጓሚዎቹ አንዱ እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፦ “ይህ መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱ ይሖዋ ሰዎችን ምን ያህል እንደሚወድና ስለ እሱ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ እንደሚፈልግ አስታውሶኛል።”
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይህን በረከት በማግኘታቸው የደስታቸው ተካፋዮች ነን። በእነዚህ ትክክለኛ ትርጉሞች አማካኝነት የይሖዋን ትእዛዛት እንደ ውድ ሀብት አድርገው መመልከታቸውን እንደሚቀጥሉ እምነታችን ነው።—ምሳሌ 2:1
a በናሚቢያ የሚከናወነውን ሥራ የሚከታተለው የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ነው።