በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ነሐሴ 19, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና

ዴቢ በተባለው አውሎ ነፋስ የተነሳ የሰሜን አሜሪካ ምሥራቃዊ ዳርቻ በጎርፍ ተጥለቀለቀ

ዴቢ በተባለው አውሎ ነፋስ የተነሳ የሰሜን አሜሪካ ምሥራቃዊ ዳርቻ በጎርፍ ተጥለቀለቀ

ነሐሴ 2024 መጀመሪያ አካባቢ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ኃይለኛ ማዕበል ተነሳ። ማዕበሉ ወዲያውኑ ኃይል ስላገኘ ዴቢ የተባለው አውሎ ነፋስ ተፈጠረ። ከዚያም ነሐሴ 5, 2024 ደረጃ 1 የተሰጠው ይህ አውሎ ነፋስ በሰዓት 130 ኪሎ ሜትር በሚከንፍ ነፋስ ስታይንሃቺ፣ ፍሎሪዳን መታ። በተጨማሪም አውሎ ነፋሱ በሚያልፍበት መንገድ ሁሉ ቢያንስ 12 የቶርኔዶ አደጋዎች (የነፋስ ማዕበሎች) እንዲከሰቱ አድርጓል። በኃይለኛው ነፋስና በከባዱ ዝናብ የተነሳ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ኤሌክትሪክ ተቋርጦባቸዋል። አሜሪካ ውስጥ ቢያንስ ስምንት ሰዎች በአደጋው ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ከዚያም አውሎ ነፋስ ዴቢ ደረጃውን ቀንሶ በስተ ሰሜን ወደ ካናዳ በዝግታ መጓዙን ቀጠለ። ዓርብ፣ ነሐሴ 9, 2024 በካናዳ በምትገኘው ኩዊቤክ ግዛት በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ 22 ሴንቲ ሜትር የደረሰ ዝናብ ጥሏል። ይህ ከባድ ዝናብ በአንዳንድ የግዛቱ ክፍሎች መኖሪያ ቤቶችን በጎርፍ አጥለቅልቋል፤ እንዲሁም በመሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል። በዚህም ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአደጋ ነፃ ወደሆኑ ቦታዎች ተፈናቅለዋል። አንዳንድ ሪፖርቶች እንደገለጹት በካናዳ አንድ ሰው በአደጋው ሞቷል።

በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት

ዩናይትድ ስቴትስ

  • በአደጋው የሞተ ወንድም ወይም እህት የለም

  • 1 አስፋፊ ጉዳት ደርሶበት ሐኪም ቤት ገብቷል

  • 23 አስፋፊዎች ተፈናቅለዋል

  • 7 መኖሪያ ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 60 መኖሪያ ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 1 የስብሰባ አዳራሽ ቀላል ጉዳት ደርሶበታል

ካናዳ

  • በአደጋው የሞተ ወንድም ወይም እህት የለም። ሆኖም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመሬት መንሸራተት የተነሳ ሕይወቱን አጥቷል

  • 1 አስፋፊ ጉዳት ደርሶበታል

  • 23 አስፋፊዎች ተፈናቅለው ነበር፤ ሆኖም አብዛኞቹ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል

  • 2 መኖሪያ ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • 165 መኖሪያ ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል

  • ጉዳት የደረሰበት ወይም የወደመ የስብሰባ አዳራሽ የለም

የእርዳታ እንቅስቃሴ

  • በዩናይትድ ስቴትስ እና በካናዳ የሚገኙ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ሽማግሌዎች በአደጋው ለተጎዱት ሁሉ መንፈሳዊና ቁሳዊ እገዛ እያደረጉ ነው

  • ካናዳ ውስጥ አንድ የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን አስፈላጊውን እርዳታ እየሰጠ ነው

በአውሎ ነፋሱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው መጸለያችንን እንቀጥላለን፤ ይሖዋ “በጭንቅ ጊዜ አዳኛችን” መሆኑን ማወቃችንም ያጽናናናል።​—ኢሳይያስ 33:2