መጋቢት 28, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና
ፍሬዲ የተባለው አውሎ ነፋስ በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ውድመት አስከተለ
ፍሬዲ የተባለው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በቅርቡ በምሥራቅ አፍሪካ ውድመት አስከትሏል፤ ፍሬዲ፣ ረጅም ጊዜ በመቆየት ሪከርዱን ከያዙት አውሎ ነፋሶች አንዱ ሆኗል። ይህ አውሎ ነፋስ የካቲት 2023 ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጉዳት አድርሷል። የካቲት 21, 2023 ማዳጋስካርን መታ፤ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ደግሞ ወደ ሞዛምቢክ ተሻግሮ ሞዛምቢክንና ማላዊን መታ። አውሎ ነፋሱ ኃይል እየጨመረ ሄዶ መጋቢት 11, 2023 በሞዛምቢክ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ጉዳት አደረሰ። በማዳጋስካር፣ በማላዊና በሞዛምቢክ የሚገኙ ብዙ ግዛቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በእነዚህ አካባቢዎች፣ ኃይለኛ ነፋስና ዶፍ ዝናብ የጎርፍ መጥለቅለቅ አስከትሏል፤ ቤቶችንም አፍርሷል። ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ጨምሮ ከ500 የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፤ በሺዎች የሚቆጠሩም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
እስከ መጋቢት 27, 2023 ድረስ የሚከተለው አጠቃላይ ሪፖርት ደርሶናል። እነዚህ አኃዞች በአካባቢው ካሉ ወንድሞች በተገኙ የተረጋገጡ ሪፖርቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ሆኖም ትክክለኛው ቁጥር ከዚህም ሊበልጥ ይችላል፤ በቀላሉ በማይደረስባቸው አካባቢዎች የጉዳቱን መጠን ለማጣራት ወንድሞች አሁንም ጥረት እያደረጉ ነው።
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
ማዳጋስካር
256 አስፋፊዎችና ሌሎች የቤተሰባቸው አባላት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል
8 መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል
29 መኖሪያ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል
3 የስብሰባ አዳራሾች ጉዳት ደርሶባቸዋል
ማላዊ
የሚያሳዝነው 8 አስፋፊዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ 6 አስፋፊዎች እስካሁን አልተገኙም
3 አስፋፊዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል
ቢያንስ 4,300 አስፋፊዎችና ሌሎች የቤተሰባቸው አባላት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል
821 መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል
174 መኖሪያ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል
20 የስብሰባ አዳራሾች ጉዳት ደርሶባቸዋል
ሞዛምቢክ
የሚያሳዝነው 1 አስፋፊ ሕይወቱን አጥቷል፤ 1 አስፋፊ እስካሁን አልተገኘም
880 አስፋፊዎችና ሌሎች የቤተሰባቸው አባላት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል
248 መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል
185 መኖሪያ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል
7 የስብሰባ አዳራሾች ጉዳት ደርሶባቸዋል
የእርዳታ እንቅስቃሴ
ጉዳት የደረሰባቸው ብዙ አካባቢዎች አሁንም ተደራሽ አይደሉም
የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች በአደጋው ለተጎዱት መጠለያ፣ ምግብ፣ ውኃና ቁሳቁሶች እያቀረቡ ነው
ሞዛምቢክ ውስጥ በጋዛ ግዛት ካምፕ ተቋቁሟል፤ ይህም በአንድ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ውስጥ ተጠልለው ለነበሩ 167 አስፋፊዎችና የቤተሰባቸው አባላት ጊዜያዊ መጠለያ ሆኗል። ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በስብሰባ አዳራሾችና በግል መኖሪያ ቤቶች እንዲያርፉ ተደርጓል
እስካሁን ድረስ ቢያንስ 16 መኖሪያ ቤቶች ተጠግነዋል
የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች እና የአካባቢው የጉባኤ ሽማግሌዎች ወንድሞች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማወቅና ማበረታቻ ለመስጠት ጉብኝት እያደረጉ ነው
በአደጋው የተጎዱት ወንድሞችና እህቶች በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም እንኳ ስብሰባዎች ለማድረግና እርስ በርስ ለመበረታታት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እያደረጉ ነው። ይሖዋ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ እንደሚሰጣቸው እንተማመናለን።—2 ቆሮንቶስ 4:7