በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥር 8, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና

2020 የአምላክ መንግሥት ዘመቻ፦ የወንድማማች ማኅበራችንን ያነቃቃ “የማይረሳ ክንውን”

2020 የአምላክ መንግሥት ዘመቻ፦ የወንድማማች ማኅበራችንን ያነቃቃ “የማይረሳ ክንውን”

ኅዳር 2020 ያካሄድነው መጠነ ሰፊ ዘመቻ በይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ውስጥ ሲታወስ የሚኖር ትልቅ ክንውን ነው። በዓለም ዙሪያ በተከሰተው ገዳይ ወረርሽኝ ሳቢያ ብዙዎቻችን እንቅስቃሴያችን ተገድቧል። ከዚህ ቀደም የምንጠቀምባቸውን የአገልግሎት ዘዴዎችም ለጊዜው ለማቋረጥ ተገድደናል። ያም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት የሚያስተዋውቅ ዓለም አቀፋዊ ዘመቻ በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ ችለዋል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች መጠበቂያ ግንብ ቁጥር 2 2020⁠ን ለንግድ ቤቶች፣ ለመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ለአስተማሪዎቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች ለማሰራጨት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ይህ ሥራ መልእክቱን ለማዳመጥ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን በሙሉ አበረታቷል። ከዚህም ሌላ በሥራው የተካፈሉ ሁሉ ይህ ነው የማይባል ደስታና መንፈሳዊ ማበረታቻ አግኝተዋል።

በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ያገኟቸውን አንዳንድ ተሞክሮዎች እንዲሁም የተናገሩትን እስቲ ሐሳብ እንመልከት፦

አውስትራሌዢያ

እህት ሉሲንዳ ፈርኪን

በአውስትራሊያ የምትኖር በቅርቡ የተጠመቀች ሉሲንዳ ፈርኪን የተባለች የ18 ዓመት ወጣት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “በዘመቻው ወቅት ከባድ የጤና ችግር አጋጥሞኝ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ እጄን ይዞ አይዞሽ እንዳለኝና ለመጽናት የሚያስችል ብርታት እንደሰጠኝ ተሰምቶኛል።”

በኒው ዚላንድ የሚኖር አንድ አባት ዘመቻው ለቤተሰቡ ያስገኘውን ጥቅም ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አራት ሴቶች ልጆች አሉን፤ ዕድሜያቸው 7፣ 9፣ 11 እና 13 ነው። ዓለም አቀፉን ዘመቻ አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሰጠን ሥራ አድርገን መቁጠራችን በየዕለቱ በአገልግሎት እንድንካፈል አነሳስቶናል።”

ቦትስዋና

በወረዳ ሥራ ላይ ያሉት ካሂሶ እና ሊዲያ ማሩሞ የመጽሔቱን ኤሌክትሮኒክ ቅጂ ለማያምኑ ዘመዶቻቸው ልከው ነበር። ብዙዎቹ ምስጋናቸውን ገልጸውላቸዋል። ሐኪም የሆነች አንዲት የካሂሶ ዘመድ መጽሔቱ የደረሳት በትክክለኛው ጊዜ እንደሆነ ተናግራለች። አንዳንድ ታካሚዎቿ ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ጥያቄ እንደነበራቸውና የራሷም ልጆች በመናፍስታዊ ድርጊቶች መካፈል እንደጀመሩ ገልጻለች። ካሂሶ እና ሊዲያ ይህችን ሴት ያነጋገሯት ሲሆን በዚያው ምሽት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀመሯት። አሁን በሳምንት ሁለት ጊዜ ያጠናሉ።

ወንድም ካሂሶ ማሩሞ ከባለቤቱ ከሊዲያ ጋር

ካናዳ

እህት ሶሮያ ቶምሰን

በኦንታሪዮ የምትኖር ሶሮያ ቶምሰን የተባለች አቅኚ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ዘመቻው፣ በጣም አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ ይበልጥ ትኩረት እንዳደርግ እና ገና ብዙ የሚቀር ሥራ መኖሩን እንድገነዘብ ረድቶኛል። በተጨማሪም ይሖዋ ሰዎችን ምን ያህል እንደሚወድ እንዲሁም ማንም ሰው እንዲጠፋ እንደማይፈልግ አስታውሶኛል። እንዲህ ያለ አመለካከት መያዜ በዘመቻው ይበልጥ በቅንዓት እንድካፈል አነሳስቶኛል።”

በብሪቲሽ ኮሎምቢያ የምትኖር አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በዚህ ውጥረት የነገሠበት ጊዜ ውስጥ አሉታዊ ስሜቶችን ለማሸነፍ ስል ረዳት አቅኚ ለመሆን ወሰንኩ። ይህን ማድረጌ ይበልጥ አዎንታዊ እንድሆን ረድቶኛል፤ ቤተሰቤንም ጠቅሟል።”

የካናዳ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ ዘመቻው ቤተሰቦች እርስ በርስ እንዲቀራረቡ እንዳደረጋቸው ገልጿል። በተጨማሪም ልጆች በአገልግሎት ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተሰምቷቸዋል፤ ምክንያቱም አጫጭር ደብዳቤዎችን ራሳቸው መጻፍ ወይም ፖስታ ላይ አድራሻ መጻፍ፣ ቴምብር መለጠፍ እንዲሁም አድራሻዎች መፈለግ ችለዋል።

ፊንላንድ

የወረዳ የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም ቲሞ ቱሚስቶ እና ባለቤቱ እንዲህ ብለዋል፦ “እኛ ባለንበት በሰሜን ዋልታ አካባቢ ኅዳር ጨለማ የሆነ ወር ነው። ስለዚህ ወንድሞችና እህቶች በተለይም አቅኚዎች በጨለማው ውስጥ ብርሃን እንዲፈነጥቅ ባደረገው በዚህ ዘመቻ በመካፈላቸው በጣም ደስተኞች ሆነዋል።”

ወንድም ቲሞ ቱሚስቶ እና ባለቤቱ ኤቫ

አንድ ባልና ሚስት መጽሔቱን ለአንድ የሚያውቁት ሰው ከላኩ በኋላ የምስጋና ደብዳቤ ደረሳቸው፤ ደብዳቤው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ዛሬ [የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን] የያዕቆብ መጽሐፍን እያነበብኩ ነበር። ጥቅሱ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ እንደሆነ ይገልጻል። የይሖዋ ምሥክሮች ሁልጊዜ ወደ ሰዎች በመሄድ መጽሐፍ ቅዱስን ለማብራራት እና ለማስተማር በሚያደርጉት ጥረት ይታወቃሉ። እምነት የሚያጠናክር ሥራ ያከናውናሉ።”

ግሪክ

የግሪክ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወረርሽኙ፣ የተጣሉት ገደቦች እንዲሁም ከቤት መውጣት አለመቻሉ ለብዙዎች አሰልቺ ሆኖባቸዋል። ዘመቻው ግን መንፈሳቸውን አድሶላቸዋል። ብዙዎች ዘመቻው እንደ በረሃ ገነት እንደሆነላቸው ገልጸዋል።”

እህት ሱዚ ጎድርዬሬ

እህት ሱዚ ጎድርዬሬ፣ የጤና እክል ያለባት ከመሆኑም ሌላ ባለቤቷ የይሖዋ ምሥክር አይደለም፤ ያም ቢሆን ረዳት አቅኚ ለመሆን ወሰነች። እንዲህ ብላለች፦ “ዘመቻው አሉታዊ ስሜቶቼን በሙሉ አስወግዶልኛል። ጠዋት ከእንቅልፌ ደስ ብሎኝ እነሳለሁ፣ የቤት ውስጥ ሥራዎቼን አከናውናለሁ፣ ምግብ አበስላለሁ፣ ለባለቤቴ ቁርስ አቀርባለሁ፤ ከዚያም አገልግሎቴን እጀምራለሁ። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ባለቤቴ ከእህቶች ጋር ብዙ ጊዜ በደስታ ሳገለግል ስለሚያየኝ አንዳንድ ጊዜ ‘ዛሬ አገልግሎት የለሽም?’ ብሎ ይጠይቀኛል።”

ጃፓን

እህት ታማኪ ሂሮታ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ደብዳቤ ትጽፍ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “በደብዳቤ በመመሥከር ረገድ ቀዳሚው ይሖዋ ነው። ለሰው ዘር 66 ደብዳቤዎችን ጽፏል፤ ባለፉት በርካታ ዘመናት የኖሩ ሰዎች ሁሉ ወደ አምላክ ለመቅረብ ሲሉ እነዚህን ደብዳቤዎች በተደጋጋሚ አንብበዋቸዋል። ይሖዋ፣ ይህ ዘዴ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ያውቃል። በእርግጥም ዘመቻው የማይረሳ ክንውን ነበር።”

እህት ታማኪ ሂሮታ

ስሪ ላንካ

እህት ማሃራጃ ቪጄያ እና እህት ኢምያናታን አሙታ ወደ ተመሳሳይ አድራሻ ደብዳቤ እንዲጽፉ በስህተት ተመደቡ። ደብዳቤው የደረሰው ሰው የመጀመሪያውን ደብዳቤ ሳይከፍት ጣለው። ሁለተኛውን ደብዳቤ ሲመለከተው ግን ‘ደብዳቤው ሁለት ጊዜ የተላከው በጣም አስፈላጊ መልእክት ቢይዝ ነው’ ብሎ አሰበ። ስለዚህ መጽሔቱን አነበበው፤ ከዚያም ሁለተኛውን ደብዳቤ ለላከችው እህት ደወለላት፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ።

ከግራ ወደ ቀኝ፦ እህት ማሃራጃ ቪጄያ እና እህት ኢምያናታን አሙታ

አንዲት ባለሥልጣን፣ መጽሔቱ ከደረሳት በኋላ ወደ ስሪ ላንካ ቅርንጫፍ ቢሮ ደወለች። ሴትየዋ ክርስቲያን ብትሆንም የይሖዋ ምሥክሮችን ፈጽሞ አግኝታ እንደማታውቅ ገለጸች። ለመጽሔቱና ለድረ ገጻችን አድናቆቷን ከገለጸች በኋላ “እኔስ የይሖዋ ምሥክር መሆን የምችለው እንዴት ነው?” ብላ ጠየቀች። ወዲያውኑ ተመላልሶ መጠየቅ እንዲደረግላት ዝግጅት ተደረገ።

ዩናይትድ ስቴትስ

አንድ የ13 ዓመት ልጅ በሚማርበት ትምህርት ቤት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ብዙ ጊዜ ይነሱ ነበር፤ ይህ አስፋፊ የኅዳሩ ዘመቻ እንዴት እንደረዳው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ የሆንኩት ለምን እንደሆነ ለአስተማሪዎች ይበልጥ በድፍረት መናገር ችያለሁ። ይህም እምነቴን ይበልጥ አጠናክሮልኛል።”

እህት ማርጊት ሄሪንግ

እህት ማርጊት ሄሪንግ ተመሳሳይ ሐሳብ አላት። እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ድፍረቴ እና ቅንዓቴ ይበልጥ ጨምሯል። ለንግድ ቤቶች እና ለመንግሥት ባለሥልጣናት መስበክ መጀመሪያ ላይ አስፈርቶኝ ነበር። በገርነት ለእምነቴ ጥብቅና መቆም የምችለው እንዴት እንደሆነ መማሬ ለወደፊቱም ይጠቅመኛል።”

አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ወንድሞችና እህቶች ከባድ የጤና እክል ቢኖርባቸውም በአቅኚነት መካፈላቸው በጣም አበረታቶኛል። ‘አቅሜ አይፈቅድም’ ማለት ይችሉ ነበር። እነሱ ግን በዘመቻው ለመካፈል ወስነዋል። የተሰማቸውን ደስታ እንዲሁም ለይሖዋ እና ለወንድሞቻቸው ያላቸውን አድናቆት ሲገልጹ የሰሙ ብዙዎች እንባቸውን መቆጣጠር አቅቷቸዋል።”

ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ሌሎች በርካታ ተሞክሮዎች እና የአድናቆት መግለጫዎች አሉ፤ ሁሉንም ለማስፈር ቦታ አይበቃንም። በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ማድረስ በመቻላችን በጣም ተደስተናል።—ዮሐንስ 15:11