ሰኔ 17, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና
JW ላይብረሪ ላይ የሚገኘው የምርምር መርጃ መሣሪያ ሰፋ ያለ የጥቅሶች ማውጫ ይዞ ወጣ
የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች፣ ሚያዝያ 25, 2022 JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ላይ ተሻሽሎ ወጣ። የጥቅሶችን ማብራሪያ የያዘው ማውጫ ተጨማሪ ማመሣከሪያ ጽሑፎች እንዲያካትት ተደርጓል።
ማሻሻያው ምን አዲስ ነገር አለው?
በ2013 ከወጣበት ጊዜ አንስቶ የምርምር መርጃ መሣሪያ የቅርብ ጊዜ ጽሑፎችን የሚያመሣክር የጥቅሶች ማውጫ ነበረው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርካታ ቆየት ያሉ ጽሑፎች JW ላይብረሪ ላይ እንዲካተቱ ተደርጓል። የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት ላይ ከሚገኙት ጽሑፎች አብዛኞቹ በአሁኑ ወቅት JW ላይብረሪ አፕሊኬሽንም ላይ ይገኛሉ። ተሻሽሎ የወጣው የምርምር መርጃ መሣሪያ እነዚህን ቆየት ያሉ ጽሑፎች ማመሣከሪያ አድርጎ አካትቷል፤ ከእነዚህ አንዱ፣ ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተሰኘው ጽሑፍ ነው። JW ላይብረሪ ላይ የሚገኘው የምርምር መርጃ መሣሪያ፣ የማመሣከሪያ ጽሑፎቹ የያዙትን ሐሳብም አካትቷል፤ ይህም ከኢንተርኔት ጋር መገናኘት ሳያስፈልግ የማመሣከሪያ ጽሑፎቹ ላይ ያለውን ሐሳብ ለማንበብ ያስችላል።
በዚህ ማሻሻያ ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! ወደተባለው መጽሐፍ የሚመሩ ማመሣከሪያዎችም ተካትተዋል። ካሪ የተባለች እህት ያስተዋለችውን ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በስልክ መመሥከር ያስፈራኛል፤ ሆኖም ሰዎች መጽናኛ በጣም እንደሚያስፈልጋቸው አውቃለሁ። አንዳንድ ጊዜ አንድ ጥቅስ ወደ አእምሮዬ ይመጣል፤ ሆኖም ጥቅሱን ቀላልና ማራኪ በሆነ እንዲሁም ለተጨማሪ ውይይት በር በሚከፍት መንገድ ማብራራት የምችለው እንዴት እንደሆነ ግራ ይገባኛል። አሁን ግን ማድረግ የሚጠበቅብኝ የምርምር መርጃ መሣሪያ ላይ ገብቼ ጥቅሱን መንካት ብቻ ነው፤ ከዚያም ለዘላለም በደስታ ኑር! መጽሐፍን ጨምሮ ጥቅሱን የሚያብራሩ የተለያዩ የማመሣከሪያ ጽሑፎች ይወጡልኛል። ይህ ዝግጅት በአገልግሎት ላይ ይበልጥ ደፋርና ደስተኛ እንድሆን ረድቶኛል።”
ሌሎች በርካታ ቋንቋዎች የምርምር መርጃ መሣሪያ እንዲኖራቸው ሲባል ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት የሚጠይቀው አሠራር ቀላል እንዲሆን ተደርጓል። በቺሊ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግለው ኢቮ እንዲህ ብሏል፦ “የምርምር መርጃ መሣሪያ በማፑዱንጉን ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው አሁን ነው። ይህን ጽሑፍ በማዘጋጀቱ ሥራ ስካፈል ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው፤ አሠራሩ ግን ቀላል ስለሆነ አልከበደኝም። ወንድሞች በቋንቋችን ይህ ጽሑፍ መውጣቱን ሲያዩ በጣም ነው የተገረሙት። ያን ያህል ብዙ ጽሑፍ በሌለው ቋንቋ የምርምር መርጃ መሣሪያ ይወጣል ብለው አልጠበቁም ነበር። ለግል ጥናትም ሆነ በጉባኤ ላይ ሐሳብ ለመስጠትና ንግግር ለመዘጋጀት የሚረዳ ጠቃሚ መሣሪያ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል።”
የምርምር መርጃ መሣሪያ የጥቅሶች ማውጫ አጠቃቀም
መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምርምር ልታደርግበት የፈለግከውን ጥቅስ ክፈት።
ቁጥሩን ጠቅ አድርግ። በዚህ ጊዜ መምረጫ ይወጣልሃል፤ የምርምር መርጃ መሣሪያን የሚያሳየውን ምስል ምረጥ። መምረጫው ላይ የምርምር መርጃ መሣሪያን የሚያሳየውን ምስል ካጣኸው ይህን ጥቅስ የሚያብራራ ማመሣከሪያ ጽሑፍ የምርምር መርጃ መሣሪያው ላይ የለም ማለት ነው።
የምርምር መርጃ መሣሪያ መጀመሪያ ላይ የሚዘረዝረው ቅርብ ጊዜ የወጡ ጽሑፎችን ነው። ቆየት ያሉትን ማመሣከሪያ ጽሑፎች ማግኘት ከፈለግህ ወደ ታች ወርደህ ፈልግ። የመረጥከው ጥቅስ፣ የግንዛቤ ማስተካከያ የተደረገበት ከሆነ ወቅታዊ የሆነውን ማብራሪያ የምታገኘው በተጠቀሱት የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች ላይ ነው።