በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

JW ስትሪም ስቱዲዮ አስፋፊዎች (በስተግራ) በአካባቢያቸው ያሉ ተናጋሪዎች (በስተቀኝ) የወረዳ ስብሰባ ንግግሮችን ሲያቀርቡ በቀጥታ እንዲከታተሉ ያስችላል

ሚያዝያ 1, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና

JW ስትሪም ስቱዲዮ ተጀመረ

JW ስትሪም ስቱዲዮ ተጀመረ

አሁን አስፋፊዎች በአካባቢያቸው የሚደረገውን የወረዳ ስብሰባ በቀጥታ መከታተል ይችላሉ

የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የሚገኝበትን የወረዳ ስብሰባ በቀጥታ ለማሰራጨት የሚያስችል JW ስትሪም ስቱዲዮ የተባለ አዲስ ድረ ገጽ በቅርቡ ከፍተዋል። መጋቢት 6 እና 7, 2021 ላይ ይህን ዘዴ በመጠቀም በዓለም ዙሪያ 340 የወረዳ ስብሰባዎች ተካሂደዋል። ከ500,000 የሚበልጡ ሰዎች ፕሮግራሞቹን ተከታትለዋል።

በየአካባቢው ያሉ የተመደቡ ወንድሞች ለእያንዳንዱ የወረዳ ስብሰባ የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋሉ

ወረርሽኙ ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ የበላይ አካሉ የትምህርት ኮሚቴ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች በኢንተርኔት አማካኝነት የወረዳ ስብሰባዎችን በቀጥታ ማስተላለፍ የሚችሉበት ድረ ገጽ እንዲሠራ በዋናው መሥሪያ ቤት ለሚገኘው የብሮድካስቲንግ ክፍል መመሪያ ሰጠ። ዓላማው በሺዎች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ፕሮግራሞችን በቀጥታ መከታተል እንዲችሉ ማድረግ ነው።

የብሮድካስቲንግ ክፍሉ ጥቂት ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ አነስተኛ ቡድን በዚህ ፕሮጀክት ላይ እንዲሠራ መደበ። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ተፈታታኝ ለሆኑ የተለያዩ ችግሮች መፍትሔ ማግኘት ነበረባቸው።

ለምሳሌ ያህል፣ ድረ ገጹን የሚጠቀሙት የተለያየ የቴክኒክ ችሎታ ያላቸው ወንድሞች ስለሆኑ ድረ ገጹ ለአጠቃቀም ቀላል መሆን ነበረበት። በተጨማሪም ዝቅተኛ በሆነ የኢንተርኔት አገልግሎትም በደንብ መሥራት ያስፈልገው ነበር። ከዚህም ሌላ የብሮድካስቲንግ ክፍሉ በድረ ገጹ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን የኢንተርኔት መጨናነቅ ሊያስተናግዱ የሚችሉ በቂ የኮምፒውተር ሰርቨሮች ለማግኘት በዋናው መሥሪያ ቤት ከሚገኘው የኮምፒውተር ክፍል ጋር ተባብሮ መሥራት አስፈልጎታል።

በብሮድካስቲንግ ክፍል የሚያገለግለው አሌክስ ኸርናንዴዝ “በመቶዎች የሚቆጠሩ የወረዳ ስብሰባዎችን በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ማስተላለፍ የሚችል ድረ ገጽ መሥራት አስደሳች ሆኖም ፈታኝ ነው” በማለት ተናግሯል። አክሎም “ቡድናችን ጥቂት ፕሮግራመሮችን ያቀፈ አነስተኛ ቡድን ነው፤ አብዛኞቹ ደግሞ የቀጥታ ስርጭት ፕሮግራም ለማስተላለፍ የሚያስችል ድረ ገጽ ሲሠሩ መጀመሪያቸው ነበር” ብሏል።

የመጀመሪያው የ​JW ስትሪም ስቱዲዮ ንድፍ የተጠናቀቀው ግንቦት 2020 ነው። ከአምስት ወራት በኋላ ማለትም ጥቅምት 2020 ላይ የብሮድካስቲንግ ክፍሉ በስድስት የተለያዩ አገሮች ካሉ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጋር በመተባበር ድረ ገጹን መሞከር ጀመረ። ይህ ሙከራ የብሮድካስቲንግ ክፍሉ ድረ ገጹ ከመከፈቱ በፊት፣ ያሉበትን ችግሮች ለይቶ እንዲያውቅና እንዲፈታ አስችሎታል። ድረ ገጹ በዓለም ዙሪያ ክፍት በተደረገበት ጊዜ ደግሞ የቴክኒክ ድጋፍ የሚያበረክት 17 ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ ቡድን ተቋቁሞ ነበር።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው የወንድም አማዲዝ ቤተሰብ በ​JW ስትሪም ስቱዲዮ የሚተላለፈው የወረዳ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት ፎቶ ሲነሳ

በተጨማሪም አሌክስ እንዲህ ብሏል፦ “የሆነ እንቅፋት ሲያጋጥመን ሥራችንን አቁመን ስለ ጉዳዩ እንጸልያለን። ለችግሩ መፍትሔ ስናገኝ ይሖዋ እየረዳን እንዳለ እርግጠኞች እንሆናለን።”

በርካታ ወንድሞችና እህቶች ከወዲሁ ለዚህ ዝግጅት ያላቸውን አድናቆት እየገለጹ ነው።

በኮሎምቢያ የሚኖረው ወንድም ሃይሮ ኤስፒኖሳ እንዲህ ብሏል፦ “በ​JW ስትሪም ስቱዲዮ የተላለፈው የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም ክርስቲያናዊ አንድነታችንን እንዳጠናከረውና ከወንድሞቻችን ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ እንደረዳን ተሰምቶናል። በተጨማሪም ፕሮግራሙ በቀጥታ እየተላለፈ እንዳለ ማወቃችን ንግግሮቹን በትኩረት እንድንከታተል ረድቶናል። ምንም ነገር እንዲያመልጠን አልፈለግንም፤ ይህ ዝግጅት የይሖዋ በረከት ነው!”

በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው እህት ማጋሊ ሬሙንዶ እንዲህ ብላለች፦ “በቀጥታ የሚተላለፈው ፕሮግራም ላይ የሚቀርበው ትምህርት አስቀድሞ በተቀዳው ፕሮግራም ላይ ከሚተላለፈው ትምህርት የተለየ እንዳልሆነ አውቃለሁ፤ የማውቃቸው ሰዎች ንግግሩን በቀጥታ ሲሰጡ ማየት መቻሌ ግን በጣም አስደስቶኛል።”

JW ስትሪም ስቱዲዮ እስካሁን ከ800 የሚበልጡ የወረዳ ስብሰባዎችን ለማስተላለፍ አገልግሏል። ይሖዋ በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድንሆንና አንድነታችንን እንድንጠብቅ የሚረዳ ተጨማሪ መሣሪያ ስለሰጠን ከልብ እናመሰግነዋለን።—መዝሙር 133:1