በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 11, 2019
ዓለም አቀፋዊ ዜና

JW ብሮድካስቲንግ አምስት ዓመት ሞላው

JW ብሮድካስቲንግ አምስት ዓመት ሞላው

ላለፉት አምስት ዓመታት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞቻችን በ​JW ብሮድካስቲንግ አማካኝነት በየወሩ መንፈሳዊ ፕሮግራሞችን ሲከታተሉ ቆይተዋል። በ2020 የአገልግሎት ዓመትና ከዚያ በኋላ የሚቀርቡልንን ፕሮግራሞች ለመመልከት በጉጉት እንጠብቃለን። አሁን ግን በጥቅምት 2014 ከቀረበው የመጀመሪያ ፕሮግራም አንስቶ የተደረጉትን አንዳንድ ማሻሻያዎች እንመልከት።

ወደ 185 ቋንቋዎች ይተረጎማል። መጀመሪያ ላይ ወርሃዊ ፕሮግራሙ የሚቀርበው በእንግሊዝኛ ብቻ ነበር። ግንቦት 2015 ግን የበላይ አካሉ ፕሮግራሞቹ ከ40 ወደሚበልጡ ቋንቋዎች እንዲተረጎሙ ፈቃድ ሰጠ። ይህ ዝግጅት ከተጀመረ አራት ዓመት ያለፈው ሲሆን በአሁኑ ወቅት JW ብሮድካስቲንግ በአማካይ ወደ 185 ቋንቋዎች ይተረጎማል።

ዓለም አቀፋዊ ይዘት። ፕሮግራሞቹ የሚዘጋጁት ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር እንደመሆኑ መጠን ለወርሃዊው ፕሮግራም የሚሆኑ ቪዲዮዎችን የሚያዘጋጁት በተለያዩ አገራት የሚገኙ የቪዲዮ ቡድኖች ናቸው። ወርሃዊ ፕሮግራሞቹ አብዛኛውን ጊዜ የሚደመደሙት ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ጉባኤዎችን በማሳየት ነው፤ እስካሁን ሞንጎሊያን፣ ሳይፓንን፣ ቱቫሉን፣ አይስላንድን፣ ኡጋንዳንና ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች ታይተዋል። JW ብሮድካስቲንግ ላይ የሚወጡ ቪዲዮዎች በ230 አገሮች ውስጥ ይታያሉ፤ ከእነዚህም መካከል በአንታርክቲካ አቅራቢያ የሚገኙትን ቋሚ ነዋሪ የሌላቸውን ኸርድ ደሴት እና ማክዶናልድ ደሴቶች ጨምሮ ገለልተኛ የሆኑ አካባቢዎች ይገኙበታል። አዲስ ብሮድካስት ከወጣ በኋላ ባለው በመጀመሪያው ወር ውስጥ በአማካይ 8.6 ሚሊዮን ጊዜ ይታያል ወይም ይወርዳል።

በዓይነትና በብዛት የቀረበ። እስካሁን ድረስ ንግግሮችን፣ ቃለ ምልልሶችን፣ ዜናዎችንና አጫጭር ድራማዎችን ጨምሮ በድምሩ ከ60 ሰዓት በላይ ርዝመት ያላቸው ፕሮግራሞች ተዘጋጅተዋል። ዘ ቤስት ላይፍ ኤቨር የሚል ርዕስ ያለው የመጀመሪያው ኦሪጅናል ሙዚቃ ከወጣ በኋላ በወርሃዊ ፕሮግራሞቹ ላይ የሙዚቃ ቪዲዮ በቋሚነት ተካቷል። እነዚህ መዝሙሮች ወደ 368 ቋንቋዎች ይተረጎማሉ።

የፕሮግራሙ መሪዎች። መጀመሪያ ላይ ሁሉንም ፕሮግራሞች የሚመሩት የበላይ አካል አባላት ብቻ ነበሩ። በኋላ ግን የበላይ አካል ኮሚቴ ረዳቶች ከበላይ አካል አባላት ጋር አብረው ወይም ለብቻቸው ፕሮግራሙን መምራት ጀመሩ። በድምሩ 29 ወንድሞች ፕሮግራሞቹን መርተዋል።

የአድናቆት መግለጫዎች። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ ወንድም አንጎሉ ውስጥ ደም ፈስሶ የነበረ ሲሆን አሁንም ሙሉ በሙሉ አላገገመም፤ ይህ ወንድም በተለይ ኦሪጅናል መዝሙሮቹን በጣም እንደሚወዳቸው ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው እነዚህ አስደሳች መዝሙሮች አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበርና ያጋጠመኝን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመቋቋም አስችለውኛል። ሙዚቃዎቹ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ይበልጥ ለማዳበር በእጅጉ ረድተውኛል። ለዚህ ዝግጅት በጣም አመሰግናችኋለሁ!”

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ትንሽ ልጃቸው በካንሰር የሞተባቸው ወላጆች የኅዳር 2016ን ብሮድካስት ከተመለከቱ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ጀስት አራውንድ ዘ ኮርነር የሚለውን የሙዚቃ ቪዲዮ ስናይ እንባችንን መቆጣጠር አልቻልንም። በቪዲዮው ላይ በገነት ውስጥ ያሉትን ወላጆች ስንመለከት በእነሱ ቦታ ራሳችንን ሥለን ነበር። ሐዘን ከአቅማችን በላይ እንደሆነብን በሚሰማን ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ስሜታችንን እንደሚረዳልንና ሐዘናችንን እንድንቋቋም እንደሚረዳን ያስታውሰናል። ያ ቪዲዮ ይሖዋ ለጸሎታችን የሰጠን መልስ እንደሆነ ተሰምቶናል።”

በዩክሬን የሚኖሩ ባልና ሚስት “JW ብሮድካስቲንግ የበላይ አካል አባላት የቤተሰባችን አባላት እንደሆኑ እንዲሰማን አድርጎናል” በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ይሖዋ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሕዝቦቹን አንድ ለማድረግ ሲል ይህን ወቅታዊ ዝግጅት ስላደረገልን እናመሰግነዋለን።—1 ጴጥሮስ 2:17