ሚያዝያ 9, 2021
ዓለም አቀፋዊ ዜና
JW ዜና ላይ የሚወጡት ርዕሶች በመላው ዓለም ያሉ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እያበረታታቸውና አንድነታቸውን እያጠናከረ ነው
ስደት እየደረሰባቸው ስላሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚገልጹት JW ዜና ላይ የሚወጡ ርዕሶች እንድንጸና ይረዱናል። ታሪካቸውን በአጭሩ የሚገልጹት ሐሳቦች ስለ እነሱ እንድናውቅ ያስችሉናል፤ ተሞክሮዎቻቸውና የሰጧቸው ሐሳቦች ደግሞ የሚያበረታቱንና አንድነታችንን የሚያጠናክሩልን ከመሆኑም ሌላ ደስታቸውን ጠብቀው እየጸኑ እንዳለ እንድንተማመን ያደርጉናል። ከዚህ በታች የተጠቀሱት ተሞክሮዎች በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ከእነዚህ ርዕሶች ጥቅም እያገኙ ያሉት እንዴት እንደሆነ ያሳያሉ።
ማድረግ በምንችለው ነገር ላይ ማተኮር
ወንድም ሚጌል ሲልቫ እና ባለቤቱ ሞኒካ (ከላይ የሚታዩት) በፖርቱጋል ልዩ አቅኚ ሆነው ያገለግላሉ፤ እንደ ብዙዎቻችን ሁሉ በወረርሽኙ የተነሳ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ተቀይሯል። ይህም በስሜታቸው ላይ ከባድ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም JW ዜና ላይ የወጣውን ስለ ወንድም ኮንስታንቲን ባዠኖቭ የሚገልጸውን ሪፖርት ሲያነቡ ተበረታቱ። ወንድም ኮንስታንቲን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ቢፈልግም እስር ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት አልቻለም። ያም ቢሆን ባጋጠመው ሁኔታ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ የሚያስታውሳቸውን ጥቅሶች ተጠቅሞ የራሱን “መጽሐፍ ቅዱስ” አዘጋጀ። ኮንስታንቲን ያደረገው ነገር ሚጌልንና ሞኒካን ትልቅ ነገር አስተምሯቸዋል። ሚጌል “በወረርሽኙ ምክንያት ማድረግ ባልቻልናቸው ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ማድረግ በምንችላቸው ነገሮች ላይ ለማተኮርና ያሉንን ነገሮች ለማድነቅ ጥረት እናደርጋለን” ብሏል።
ከዚህም ሌላ ሚጌልና ሞኒካ በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብና ለማሰላሰል ተጨማሪ ጊዜ መድበዋል። ሞኒካ “ይሖዋ ያነበብነውን ነገር በሚያስፈልገን ጊዜ እንድናስታውስ እንደሚረዳን እርግጠኞች ነን” ብላለች። ሚጌል አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “የወንድም ኮንስታንቲን ተሞክሮ በወረርሽኙ የተነሳ ከቤት የማንወጣበትን ይህን ጊዜ ሌሎችን ለማበረታታት፣ ይሖዋን በመዝሙር ለማወደስና የጸሎታችንን ይዘት ለማሻሻል እንድንነሳሳ አስችሎናል።”
ከስደት ጋር በተያያዘ የሚሰማንን ፍርሃት ማሸነፍ
በካሜሩን የዘወትር አቅኚ ሆና የምታገለግለው እህት ክርስቲን ሙሂማ ኤቶንዴ ለብዙ ዓመታት ስለ ስደት የሚገልጹ ዘገባዎችን ማንበብ ፍርሃት ያሳድርባት እንደነበር በሐቀኝነት ተናግራለች። ሆኖም አመለካከቷን እንድታስተካክል የረዳት ምን እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “JW ዜና ላይ ስደት እየደረሰባቸው ስላሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚገልጹ ርዕሶችን ማንበቤ አመለካከቴን ሙሉ በሙሉ እንድለውጥ ረድቶኛል። በየትኛውም የዕድሜ ክልል ያሉ ወንድሞቼ ያላቸውን አመለካከት፣ የሚያቀርቡትን ጸሎት፣ ፈገግታቸውን እንዲሁም አስቀድመው ራሳቸውን ለስደት የሚያዘጋጁበትን መንገድ ስመለከት ይሖዋን ይበልጥ ለማወቅ ተነሳስቻለሁ። አሁን ለእሱ ያለኝ ፍቅር በጣም ስለጨመረ ስደትን ያለፍርሃት መጋፈጥ እንደምችል ይሰማኛል። ስደት በሚያጋጥመኝ ጊዜ፣ ደስተኛ ሆኜ ወደ ይሖዋ ስጸልይና ስለ እሱ ሳሰላስል በዓይነ ሕሊናዬ ይታየኛል።”
ለእምነታችን ጥብቅና ለመቆም መዘጋጀት
በሩማንያ የሚኖሩት ወንድም ዩሊያን ኒስቶር እና ባለቤቱ ኡዋና፣ ወንድም አናቶሊ ቶካሬቭ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ለእምነቱ እንዴት ጥብቅና እንደቆመ ሲያውቁ ልባቸው በጣም ተነክቷል። ወንድም አናቶሊ ተረጋግቶ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሐሳቡን የሚገልጸው በአክብሮት ነበር፤ በተጨማሪም ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ ቆርጦ ነበር። የእሱ ምሳሌ ዩሊያንና ኡዋና ችሎት ፊት ቢቀርቡ ለእምነታቸው እንዴት ጥብቅና እንደሚቆሙ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ኡዋና እንዲህ ብላለች፦ “የቤተሰብ አምልኮ ስናደርግ፣ ችሎት ፊት ለእምነታችን እንዴት ጥብቅና መቆም እንደምንችል ተለማመድን። ወንድማችን እንዳደረገው የምናምንበትን ነገር በዘዴና በአክብሮት መግለጽ ቀላል እንዳልሆነ መገንዘብ ችለናል። የቤተሰብ አምልኳችንን ስንጨርስ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ይበልጥ እንደተቀራረብን ተሰምቶናል። በተጨማሪም ለእምነታችን ጥብቅና ለመቆም ከወዲሁ መዘጋጀታችንና የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን በመጠራታችን ኩራት የሚሰማን ለምን እንደሆነ ማስታወሳችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝበናል።”
የጸሎታችንን ይዘት መመርመር
በማዳጋስካር የምትኖረው እህት አና ራቮጄርሰን የጸሎቷን ይዘት መለስ ብላ ለመመርመር ተነሳስታለች። አና የወንድም ጆቪዶን ቦቦጆኖቭን ተሞክሮ ካነበበች በኋላ እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “አንዳንድ ጊዜ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች በጣም ስለምጠመድ በዘልማድ ነው የምጸልየው። ለይሖዋ መንገር የምፈልገውን ነገር ጥቂት ደቂቃዎች አስቀድሜ ካላሰብኩ ተመሳሳይ ጸሎት እንደምጸልይ አስተውያለሁ።” ወንድም ጆቪዶን በተወው ምሳሌ ላይ በደንብ ካሰላሰለች በኋላ ራሷን በእሱ ቦታ አድርጋ ለማሰብ ሞከረች። አና ‘እኔ የእሱ ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመኝ እሱ የጠቀሳቸውን ነገሮች ለይቼ እጠቅሳለሁ?’ ብላ ራሷን ጠየቀች። እንዲህ ብላለች፦ “እንዲህ ማድረጌ ከመጸለዬ በፊት የተወሰነ ጊዜ ወስጄ ለይሖዋ መንገር የምፈልጋቸውን ነገሮች ማሰብ እንዳለብኝ አስተምሮኛል። እነዚህ ሪፖርቶች በመውጣታቸው በጣም አመስጋኝ ነኝ።”
ለወንድሞቻችን ይበልጥ ርኅራኄ ማሳየት
በፖርቱጋል የዘወትር አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉት ወንድም ሩበን ካታሪኖ እና ባለቤቱ አንድሪያ ከወንድሞቻቸው ጋር ይበልጥ እንደተቀራረቡ ይሰማቸዋል። ሩበን እንዲህ ብሏል፦ “ባለፉት ጊዜያት በሌሎች አገሮች ያሉ ወንድሞቻችን ስደት እየደረሰባቸው እንዳለ ብናውቅም ስለ እነሱ ብዙም የምናውቀው ነገር አልነበረም። እነማን እንደሆኑ፣ ሕይወታቸው ምን እንደሚመስል ወይም ምን ፈተና እንዳሳለፉ አናውቅም ነበር። አሁን ግን በእነዚህ ርዕሶች የተነሳ ስለ እነሱ ብዙ አውቀናል። እነሱን ለይተን በመጥቀስ ያጋጠማቸውን ሁኔታ መወጣት እንዲችሉ መጸለይ እንችላለን። ይህም ከወንድሞቻችን ጋር ይበልጥ እንድንቀራረብ እንዲሁም ጸሎታችን የበለጠ ኃይል ሊኖረው እንደሚችል እንዲሰማን አድርጓል።”
የግል ጥናት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ
ብዙዎቻችን በፖርቱጋል የዘወትር አቅኚ ሆና የምታገለግለው እህት ሲሲሊያ ካርዶሶ የተሰማት ዓይነት ስሜት ይሰማናል፤ እንዲህ ብላለች፦ “በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰው ነገር የግል ጥናት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንድገነዘብ ረድቶኛል። መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ማጥናቴ በይሖዋ ይበልጥ እንድታመንና ለእሱ ያለኝ ፍቅር እንዲጨምር አድርጓል። ይሖዋ የሚሰማኝን ፍርሃት እንዳሸንፍ ይረዳኛል። ፍርሃት የሚያሽመደምደን በይሖዋ መታመን ስናቆም ብቻ እንደሆነ ተምሬያለሁ።”
ድፍረትና እምነት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ በዘመናችን ያሉ ወንድሞችና እህቶች ታሪክ jw.org ላይ በመውጣቱ በጣም አመስጋኞች ነን። እነዚህ ታሪኮች “በሙሉ ልብ ‘ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?’” ብለን እንድንናገር ይረዱናል።—ዕብራውያን 13:6