መጋቢት 3, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና
ኮሮና ቫይረስ—መረጃ እና ክትትል
የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (COVID-19 የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል) ወረርሽኝን በቅርበት እየተከታተለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ቸነፈር እንደሚከሰት አስቀድሞ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) ወረርሽኝ ሲከሰት ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ከበሽታ ለመጠበቅ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰዳችን ጠቃሚ ነው።—ምሳሌ 22:3
አንዳንዶች በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ማወቅ ይፈልጉ ይሆናል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በደቡብ ኮሪያ፣ በጃፓን፣ በጣሊያን እንዲሁም በሌሎች አገሮች ውስጥ ባሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎችና ጉባኤዎች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል። በአንዳንድ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ጎብኚዎችና ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ሰዎች ወደ ቤቴል እንዳይገቡ ተደርጓል። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ መንግሥት ሕዝባዊ ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ በመከልከሉ፣ ቅርንጫፍ ቢሮዎች የወረዳ ስብሰባዎችን ለመሰረዝ ተገደዋል። ከዚህም ሌላ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ያሉ ጉባኤዎች ከአገልግሎትና ከጉባኤ ስብሰባዎች ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ማስተካከያዎችን አድርገዋል። በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ወንድሞቻችን ራሳቸውን በመንፈሳዊ እየተመገቡና እርስ በርስ እየተበረታቱ ነው።—ይሁዳ 20, 21
በሽታው በተከሰተባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞች ከዚህ በታች የቀረቡትን ምክሮች ጠቃሚ ሆነው አግኝተዋቸዋል። እናንተ በምትኖሩበት አካባቢ ወረርሽኝ ቢከሰት፣ እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ ማድረጋችሁ እናንተንም ሆነ ቤተሰባችሁን ሊጠቅማችሁ ይችላል።
አትሸበሩ። ወረርሽኞችን በንቃት መከታተልና ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም በእውነታው ላይ እንጂ በፍርሃት ላይ የተመሠረተ እርምጃ መውሰድ አይኖርባችሁም።—ምሳሌ 14:15፤ ኢሳይያስ 30:15
መንግሥት የሚሰጠውን መመሪያና ማሳሰቢያ ተከተሉ። መንግሥት ለኅብረተሰቡ ጤና ሲባል ቅድመ ጥንቃቄ እንድናደርግ ማሳሰቢያ ሊያስተላልፍ ወይም አንዳንድ ገደቦችን ሊጥል ይችላል። መንግሥት የሚሰጠውን መመሪያ ተከታትሎ ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ ነው።
ንጽሕናችሁን ጠብቁ። ምንጊዜም እጃችሁን በሳሙናና በውኃ መታጠብ ወይም አልኮል ባለው የእጅ ማጽጃ ማጽዳት በጣም ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም በቤታችንም ሆነ በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እጅ የሚበዛባቸውን ቁሳቁሶች ማጽዳታችን አስፈላጊ ነው። ከዚህም ሌላ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ወቅት ከመጨባበጥ መቆጠብ እንዳለብን የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፤ ምክንያቱም መጨባበጥ ወረርሽኙ እንዲስፋፋ ሊያደርግ ይችላል። የዓለም የጤና ድርጅት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃ ለኅብረተሰቡ አቅርቧል።
ለሌሎች ፍቅር አሳዩ። ሁላችንም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና በአገልግሎት መካፈል ያለውን ጥቅም እናውቃለን፤ ያም ቢሆን ከታመማችሁ ከቤት ባትወጡ የተሻለ ነው። እንዲህ ማድረጋችሁ በሽታው እንዳይዛመት ለማድረግ ያስችላል። በዚህ መንገድ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን እንዲሁም የይሖዋ ምሥክር ላልሆኑ ጎረቤቶቻችን ፍቅር ማሳየት እንችላለን።—ማቴዎስ 22:39
ከጉባኤ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ጊዜያዊ ማስተካከያዎችን ተከተሉ። ወረርሽኝ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች፣ ቅርንጫፍ ቢሮው ለተወሰነ ጊዜ ያህል የጉባኤ ወይም የወረዳ ስብሰባዎችን አሊያም ሌሎች ቲኦክራሲያዊ ፕሮግራሞችን መሰረዝ ሊያስፈልገው ይችላል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተስፋፋባቸው እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና ጣሊያን ባሉ አገሮችም እንዲህ ተደርጓል። የየአካባቢው ሁኔታ ሊለያይ ቢችልም ሽማግሌዎች የጉባኤው አስፋፊዎች የተቀዱ ስብሰባዎችን ቤታቸው ሆነው መከታተል እንዲችሉ ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። አስፋፊዎች በስልክ፣ በጽሑፍ መልእክት፣ በኢ-ሜይል ወይም በደብዳቤ ተጠቅመው አገልግሎታቸውን ማከናወን ይችሉ ይሆናል።
በጽሑፎቻችን ላይ የሚገኙ ተጨማሪ መረጃዎች
ከዚህ በታች የቀረቡት ጽሑፎች በሽታን ለመከላከል የሚረዱ ጠቃሚ ምክሮችን ይዘዋል።