በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 24, 2023
ዚምባብዌ

በዚምባብዌ የ2023 የግብርና አውደ ርዕይ ላይ የተሰጠ ምሥክርነት

በዚምባብዌ የ2023 የግብርና አውደ ርዕይ ላይ የተሰጠ ምሥክርነት

ከነሐሴ 28 እስከ መስከረም 2, 2023 የዚምባብዌ የግብርና አውደ ርዕይ በሐራሬ፣ ዚምባብዌ ተካሂዷል። በዚህ ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ ላይ ከ500 በላይ ተሳታፊዎችና ከ250,000 በላይ ጎብኚዎች ተገኝተዋል። በአካባቢው ያሉ ወንድሞችና እህቶችም በአውደ ርዕዩ ላይ ጽሑፎች የሚያሳዩበት ቦታ ያዘጋጁ ሲሆን በሾና፣ በእንድቤሌ (ዚምባብዌ) እና በእንግሊዝኛ ጽሑፎችን አቅርበዋል። በአውደ ርዕዩ የተሳተፉት 79 ወንድሞችና እህቶች ወደ 6,300 ገደማ ጽሑፎችን ያበረከቱ ሲሆን 116 ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራላቸው ጠይቀዋል።

ታሙካ የተባለ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ልጅ ወንድሞች ያዘጋጁትን ማሳያ ቀረብ ብሎ ሲመለከት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና—ተግባራዊ መልሶቻቸው ጥራዝ 1 እና 2 የሚሉት መጽሐፎች ትኩረቱን ሳቡት። የይሖዋ ምሥክሮች በነፃ መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያስጠኑ ሲያውቅ ደግሞ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ይበልጥ ልታብራሩልኝ ትችላላችሁ?” በማለት ጠየቀ። እነሱም ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው ብሮሹር እንዴት እንደሚጠና አሳዩት፤ በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራለት ጠየቀ። በአቅራቢያው የሚኖር አንድ ወንድም ከታሙካ ጋር ለማጥናት ፕሮግራም ይዟል።

ሌላ ሰው ወደ ወንድሞች ቀረብ በማለት የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራቸውን የሚያከናውኑት በትሕትናና በትጋት በመሆኑ እንደሚያደንቃቸው ነገራቸው። ከወንድሞች አንዱ ማቴዎስ 28:19, 20⁠ን ካነበበለት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች ሰዎች እንዲያካፍሉ የሰጣቸውን ትእዛዝ በቁም ነገር እንደሚመለከቱት አስረዳው። ሰውየውም ‘እኔም እንዲህ ዓይነት ድፍረት ቢኖረኝ’ ብሎ እንደሚመኝ ገለጸ። ወንድም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና የጋበዘው ሲሆን ሰውየው በደስታ ተስማማ።

በአውደ ርዕዩ ላይ የተገኘች አንዲት ሴት የይሖዋ ምሥክሮች ደጎችና ሥርዓታማ በመሆናቸው እንደምታደንቃቸው ገለጸች። ወንድሞችም እንዲህ የመሰሉ ባሕርያትን እንድናንጸባርቅ የሚረዳን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችንና ምክሩን በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረጋችን እንደሆነ አብራሩላት። በቦታው የነበረች አንዲት እህት ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ አሳየቻት። ሴትየዋም ብዙ ዓይነት ጽሑፎች ያሉን በመሆኑ፣ ለጽሑፎቹ ገንዘብ ባለማስከፈላችን እንዲሁም ጽሑፎቻችን ለቤተሰብና ለወጣቶች የሚሆን ይዘት ያላቸው በመሆኑ ተደነቀች። አንዳንድ ጽሑፎችንና መጽሐፍ ቅዱስ ከመውሰዷም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች። “እስከዛሬ ድረስ ይህን የመሰለ ስጦታ ተቀብዬ አላውቅም!” ብላለች።

ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአውደ ርዕዩ ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድም ጭምር ሰብከዋል። አንድ ወንድም የጉብኝት ቦታዋን እያደራጀች ከነበረች አንዲት የአውደ ርዕዩ ተሳታፊ ጋር ውይይት ጀመረ። በዚያው ዕለት ወደ በኋላ ላይ ይኸው ወንድም ለዚህች ሴት መጽሐፍ ቅዱስና አንዳንድ ጽሑፎችን ወሰደላት። እሷም በደስታ ተቀበለችው፤ የራሷ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኖራት ደጋግማ ብትሞክርም ሊሳካላት እንዳልቻለ ነገረችው። በኋላም አንዲት እህት እንድታነጋግራት ፈቃደኛ በመሆን አድራሻዋን ሰጠች።

ራንጋናይ የተባለች እህት በአውደ ርዕዩ ላይ መሳተፏ ያሳደረባትን ስሜት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ባለፈው ዓመት በጤንነቴ ምክንያት፣ የምፈልገውን ያህል በአገልግሎት መካፈል አልቻልኩም ነበር። ነገር ግን ፈታኝ ከሆኑብኝ ነገሮች ይልቅ ባገኘኋቸው በረከቶች ላይ ማተኮር እንዳለብኝ ተምሬአለሁ። በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ የመካፈል አጋጣሚ ማግኘት ከበረከቶቹ አንዱ ነው። የሚያስፈልገኝን መጽናኛና ማበረታቻ አግኝቼበታለሁ።”

በእነዚህ ተሞክሮዎች ተደስተናል፤ ከዚምባብዌ ወንድሞቻችን ጋር ሆነን “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ” መሆኑም ያኮራናል።—1 ቆሮንቶስ 3:9