በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሚያዝያ 14, 2023
ዚምባብዌ

በዚምባብዌ ያሉ ዓይነ ስውራን “ብርሃን” አዩ

በዚምባብዌ ያሉ ዓይነ ስውራን “ብርሃን” አዩ

በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮ ከሁለት ብሔራዊ ተቋማት የአድናቆት ደብዳቤ ደርሶታል፤ ደብዳቤዎቹ የተላኩት ከዶረቲ ዳንከን የዓይነ ስውራንና የአካል ጉዳተኞች ማዕከል እንዲሁም ከዚምባብዌ ዩኒቨርሲቲ ነው። ቅርንጫፍ ቢሮው በብሬይል የተዘጋጁ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱሶችንና ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለሁለቱ ተቋማት ለግሶ ነበር። የዚምባብዌ ዩኒቨርሲቲ የላከው የምስጋና ደብዳቤ በከፊል እንዲህ ይላል፦ “የሰጣችሁን መጻሕፍት ተማሪዎቻችንን በመልካም ሥነ ምግባር ለማነጽ ይረዱናል። በጣም ጠቃሚ ሥራ እያከናወናችሁ ነው፤ ለዚህም የላቀ አድናቆት ሊቸራችሁ ይገባል።”

ዓይነ ስውራንንና የዓይን ብርሃናቸውን በከፊል ያጡ ሰዎችን እንዲረዱ የተመደቡት ልዩ አቅኚዎች። በስተ ግራ፦ ወንድም ዊላርድ ማዛሩራ እና ባለቤቱ ንዬምቤዚ። በስተ ቀኝ፦ ወንድም ቱንጉሉላ ጡቤ እና ባለቤቱ ዩኒስ

ቅርንጫፍ ቢሮው በዚምባብዌ የሚገኙትን ከ10,000 በላይ ዓይነ ስውራንና የዓይን ብርሃናቸውን በከፊል ያጡ ሰዎች ለመርዳት ከዚህ ቀደምም ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ለምሳሌ በ2017 ለእነዚህ ሰዎች ምሥራቹን ለመስበክ ልዩ ዘመቻ አካሂዷል። በዘመቻው ላይ የሚሳተፉት አስፋፊዎች ለዓይነ ስውራንና የዓይን ብርሃናቸውን በከፊል ላጡ ሰዎች ሲሰብኩ ውጤታማ እንዲሆኑ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፤ ይህን ሥልጠና እንዲሰጡ፣ ልዩ አቅኚዎች የሆኑ ሁለት ባልና ሚስት ተመድበው ነበር። እንዲህ ያለ ጥረት በመደረጉ 46 ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር የተቻለ ሲሆን ሦስቱ ተጠምቀዋል።

ከተጠመቁት አንዷ እህት ሜቪስ ቻያ ናት። ምሥራቹን የሰማችው በ2021 በስልክ ምሥክርነት ነው። ሜቪስ የዓይን ብርሃኗ እንደሚመለስላት ተስፋ በማድረግ ‘እንፈውሳለን’ ወደሚሉ ሰዎች ትሄድ ነበር፤ ሆኖም ሊፈውሷት ባላመቻላቸው ተስፋ ቆረጠች። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ዓይነ ስውራን የዓይን ብርሃናቸው እንደሚመለስላቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ስትማር ተስፋዋ ለመለመ። በሳምንት ሁለት ጊዜ ማጥናት የጀመረች ሲሆን ሚያዝያ 2022 ተጠመቀች።

ይሖዋ የዓይነ ስውራንን ዓይን የሚያበራበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን፤ እስከዚያው ድረስ ግን በአሁኑ ወቅትም እንኳ እሱን ለሚሹት ሁሉ ‘ብርሃን እና ማስተዋል’ ሲፈነጥቅ ማየት ያስደስተናል።—መዝሙር 119:130