በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በሐራሬ፣ ዚምባብዌ የሚገኘው የአሁኑ ቅርንጫፍ ቢሮ። ውስጠኛው ፎቶ፦ ቡላዋዮ ውስጥ ከነበሩት ቀደምት የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች አንዱ

ጥቅምት 3, 2023
ዚምባብዌ

የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮ ሰባ አምስተኛ ዓመቱን አስቆጠረ

የዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮ ሰባ አምስተኛ ዓመቱን አስቆጠረ

በዚምባብዌ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ መስከረም 2023 ሰባ አምስተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። በአሁኑ ወቅት ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኘው የዚምባብዌ ዋና ከተማ በሆነችው በሐራሬ ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች በዚምባብዌ የስብከት ሥራቸውን ሲጀምሩ የጉባኤ እንቅስቃሴዎችን የሚያደራጀው በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ነበር። በ1932 የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ አራት አቅኚዎችን በወቅቱ ደቡብ ሮዴዥያ ተብላ ትጠራ ወደነበረችው ወደ ዚምባብዌ ላከ። ሥራውም በፍጥነት እድገት ያሳይ ጀመር።

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ኤሪክ ኩክ፣ መርትል ታይለር፣ ፊሊስ ካይት፣ ሩቢ ብራድሊ እና ጆርጅ ብራድሊ

በአገሪቱ ብሔርተኝነትና የጦርነት መንፈስ የተንሰራፋ ሲሆን በዚህም ምክንያት ከኅዳር 1940 ጀምሮ ጽሑፎቻችንን ማስገባትና ማሰራጨት ተከለከለ። በእነዚህ ዓመታት ብዙ ወንድሞችና እህቶች ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸውን በመጠበቃቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገዋል። ሆኖም ወንድሞቻችን ምሥራቹን ሌሎች በጥበብ ማካፈላቸውን ቀጥለዋል፤ ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። ከስድስት ዓመታት በኋላ እገዳው ተነሳ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የአስፋፊዎች ቁጥር ከሦስት እጥፍ በላይ አድጎ 3,500 ደረሰ።

መስከረም 1, 1948 ይህን እያደገ ያለ ሥራ ለመደገፍ የዚምባብዌ ሁለተኛ ትልቋ ከተማ በሆነችው ቡላዋዮ ውስጥ ቅርንጫፍ ቢሮ ተቋቋመ። ወንድም ኤሪክ ኩክ የመጀመሪያው የቅርንጫፍ ቢሮ አገልጋይ ሆኖ ተመደበ። ቆየት ብሎም ከጊልያድ የተመረቁት ጆርጅ እና ሩቢ ብራድሊ፣ ፊሊስ ካይት እና መርትል ታይለር በዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲያገለግሉ ተመደቡ።

በትጋት የሚሠሩት የዚምባብዌ ቤቴል ቤተሰብ አባላት፤ ከግራ ወደ ቀኝ፦ አንድ ወንድም ለቤቴል ቤተሰብ ምግብ እያዘጋጀ፣ የዚምባብዌ ምልክት ቋንቋ ትርጉም ቡድን፣ አንዲት እህት አትክልቶችን እየተንከባከበች

በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት በዚምባብዌ የአስፋፊዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት አድጓል። ይህን በመስፋፋት ላይ ያለ ሥራ ለማደራጀት እንዲቻል አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች ተገዙ።

በዚምባብዌ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ በሚነገሩ አሥር ቋንቋዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች

አሁን በሐራሬ የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ተገንብቶ የተጠናቀቀውና ለይሖዋ አገልግሎት የተወሰነው ታኅሣሥ 1998 ነው። ቅርንጫፍ ቢሮው በሰባት ቋንቋዎች የሚከናወነውን የትርጉም ሥራ በበላይነት የሚከታተል ሲሆን በክልሉ ውስጥ ለሚገኙት 960 ጉባኤዎች ድጋፍ ይሰጣል። ከ46,000 በላይ ወንድሞችና እህቶች በአገሪቱ ውስጥ በሚከናወነው የስብከት ሥራ በንቃት ይሳተፋሉ፤ በ2023 በተከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ 120,702 ሰዎች ተገኝተዋል።

በዚምባብዌ እየታየ ባለው ከፍተኛ እድገት ተደስተናል። ይህ እድገት ይሖዋ ‘ዓይኑም ሆነ ልቡ’ ለእሱ ታማኝ በሆኑት ሰዎች ላይ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—2 ዜና መዋዕል 7:16