ኅዳር 18, 2022
ዚምባብዌ
የዚምባብዌ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖታዊ መብት የሚያከብር ውሳኔ አሳለፈ
መስከረም 29, 2022 ሙታሬ ውስጥ የሚገኘው የዚምባብዌ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለወንድም ቶቢያስ ጋባዛ፣ ወንደር ሙፖሼሪ እና ጃቡላኒ ሲትሆል ፈርዷል፤ እነዚህ ወንድሞች ከሕሊናቸው ጋር በሚጋጭ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው መድልዎ ደርሶባቸዋል።
እነዚህ ሦስት ወንድሞች በአካባቢው በሚካሄድ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲሳተፉ አንድ የመንደሩ ባለሥልጣን አስገድዷቸው ነበር፤ በኋላም ጥቅምት 2020 ወንድሞች በመንደሩ አለቃ በሚመራው ችሎት ፊት እንዲቀርቡ ተጠሩ። ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ዝናብ በወቅቱ እንዲመጣ የሙታን መናፍስትን መለመንን የሚጠይቅ ነበር፤ እያንዳንዱ የመንደሩ ነዋሪም እንዲሳተፍ ይጠበቅበታል። ወንድሞቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናቸው ይህን ለማድረግ ስለማይፈቅድላቸው በሥነ ሥርዓቱ ላይ ላለመሳተፍ ወሰኑ።
የመንደሩ አለቃ በወንድሞቻችን ላይ ፈረደባቸው፤ ፈቃደኛ እንዲሆኑ ለማስገደድ በማሰብም አስፈራራቸው። ወንድሞቻችን ቺፒንጌ ወደሚገኘው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አቤት አሉ።
ጥር 5, 2021 ፍርድ ቤቱ ለወንድሞቻችን ፈረደ። የመንደሩ ባለሥልጣናት ግን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም፤ በወንድሞቻችን ላይ ጫና ማሳደራቸውንም ቀጠሉ። ይህ እንዳይበቃ ደግሞ ሌሎች የመንደሩ ነዋሪዎችም ያገልሏቸውና ይበድሏቸው ጀመር።
ወንድሞች የሚደርስባቸው መድልዎ እየበረታ ሲሄድ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ አሉ። ፍርድ ቤቱ፣ የመንደሩ ባለሥልጣናት የወንድሞችን መብት እንደጣሱ ገለጸ። በተጨማሪም ወንድሞቻችን ሕሊናቸውን በሚያስጥስ ማንኛውም ባሕላዊ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲሳተፉ ጫና እንዳይደረግባቸው እንዲሁም ካሳ እንዲከፈላቸው ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
እነዚህ ባሕላዊ ሥነ ሥርዓቶች የሚከበሩት በመላ አገሪቱ እንደመሆኑ መጠን ይህ ብይን በዚምባብዌ የሚኖሩ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ሁሉ እንደሚጠቅም ተስፋ እናደርጋለን። ይህን ድል ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።—ምሳሌ 2:8