በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ግንቦት 22, 2024
ዚምባብዌ

የይሖዋ ምሥክሮች የቺቶንጋ (ዚምባብዌ) ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች ምሥራቹን ለማወጅ ልዩ ዘመቻ አካሄዱ

የይሖዋ ምሥክሮች የቺቶንጋ (ዚምባብዌ) ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች ምሥራቹን ለማወጅ ልዩ ዘመቻ አካሄዱ

ከሚያዝያ 13 እስከ ሚያዝያ 27, 2024 በመላው ዚምባዌ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በቺቶንጋ (ዚምባብዌ) ቋንቋ በተካሄደው ልዩ የስብከት ዘመቻ ተሳትፈዋል። በዚምባብዌ ከሚኖሩት 300,000 ገደማ የቺቶንጋ (ዚምባብዌ) ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል ብዙዎቹ የሚኖሩት በአገሪቱ ሰሜን ምዕራብ በቢንጋ ክልል ባሉ የገጠር መንደሮች ነው። በዚህ አካባቢ ለሚኖረው ለእያንዳንዱ ሰው ምሥራቹን ማድረስ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም በቺቶንጋ (ዚምባብዌ) ቋንቋ በሚመሩት ስምንት ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉት የይሖዋ ምሥክሮች ከ300 አይበልጡም።

ዘመቻው ግሩም ውጤት አስገኝቷል። በአንድ ጉባኤ ውስጥ በዘመቻው ወቅት በተካሄደው የመጀመሪያው ስብሰባ ላይ 77 ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ተገኝተዋል። በቀጣዩ ሳምንት ደግሞ 126 ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። በአጠቃላይ ከ2,000 የሚበልጡ ሰዎችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ተችሏል።

ወንድሞቻችን ወደ አንድ መንደር ሲሄዱ አንዲት ሴትና ልጆቿን አገኙ። አስፋፊዎቹ የቤቱን አባወራ ማነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጹላት። የሴትየዋ ባለቤት ሲመጣ የመንደሩ አለቃ መሆኑን ነገራቸው። ወንድሞች መጀመሪያ እሱን ለማነጋገር አስበው እስኪመጣ በመጠበቅ አክብሮት ስላሳዩት በጣም ተደሰተ። በቺቶንጋ (ዚምባብዌ) ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱሱን ይዞ መጣ፤ እነሱም መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እንደሚያስጠኑ አሳዩት። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት እንዲያጠና ቀጠሮ ያዙ። ሰውየው እሱ በሚያስተዳድራችው ሌሎች መንደሮችም እንዲሰብኩ ፈቀደላቸው።

ሁለት ወንድሞች በአንዲት ትንሽ ከተማ እየሰበኩ ሳሉ ‘የይሖዋ ምሥክር ነኝ’ የሚል አንድ ሰው አጋጠማቸው።ሰውየው በ1993 የይሖዋ ምሥክሮች አባቱን አነጋግረውት እንደነበረ ገለጸላቸው። አባትየው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ቢጀምርም ቤተሰቡ በተደጋጋሚ ጊዜያት ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወሩ ምክንያት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተጠፋፋ። ወንድሞች አባትየውን ለማግኘት ስለፈለጉ በቀጣዩ ቀን በእግራቸው አንድ ሰዓት ተኩል ተጉዘው ቤተሰቡ ወዳለበት መንደር ሄዱ። አባትየው ወንድሞችን ሲያይ በጣም ተደሰተ፤ በዚያ ዕለት እሱና ባለቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች እንዲመጡ እየጸለዩ እንደነበረ ነገራቸው። መላው ቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ፤ እንዲሁም በሳምንቱ መሃል በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ሁሉም ተገኙ። እንዲያውም አንድ ጎረቤታቸውን ይዘው መጡ።

አንዲት እህት በውኃ ቦኖ አጠገብ ለአንዲት ሴት ስትመሠክር

አሊሺያ የተባለች አንዲት እህት፣ ያነጋገረቻት አረጋዊት ሴት በጉባኤ ስብሰባ ላይ እንድትገኝ የቀረበላትን ግብዣ ምንም ሳታቅማማ ተቀበለች። አሊሺያ ወደ ስብሰባው ልትወስዳት ስትመጣ ሴትየዋ ተዘጋጅታ እየጠበቀቻት ነበር፤ አንዲት ጓደኛዋንም አብራት እንድትሄድ ጋብዛ ነበር። ከስብሰባው በኋላ አረጋዊቷ ሴት እንዲህ አለች፦ “አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። ያሳያችሁኝ ፍቅርና ያደረጋችሁልኝ ሞቅ ያለ አቀባበል ሁልጊዜ እንድመጣ አነሳስቶኛል።”

በዚምባብዌ እንዳሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሁሉ እኛም ይህ ዘመቻ ባስገኘው መልካም ውጤት ተደስተናል። በሁሉም የምድር ክፍሎች ‘ዘሩን ለመዝራት’ የምናደርገው ትጋት የተሞላበት ጥረት ስኬታማ እንደሚሆን ይህ ዘመቻ አንድ ማሳያ ነው።​—መክብብ 11:6