በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 25, 2021
ዛምቢያ

መጽሐፍ ቅዱስ በሉንዳ ቋንቋ ወጣ

መጽሐፍ ቅዱስ በሉንዳ ቋንቋ ወጣ

በሉንዳ ቋንቋ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅምት 16, 2021 በዲጂታል ፎርማት ወጣ፤ መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱ የተገለጸው በሦስት የአፍሪካ አገሮች ለሚገኙ አስፋፊዎች በተላለፈ ልዩ ፕሮግራም ላይ ነበር። የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ የካቲት 2022 ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

የዛምቢያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኢማኑኤል ቺፖሳ መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን አስቀድሞ በተቀረጸ ንግግር አማካኝነት አብስሯል። ንግግሩ በአንጎላ፣ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ እና በዛምቢያ ለሚገኙ አድማጮች ተላልፏል።

ብዙዎቹ የሉንዳ ተናጋሪዎች ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት በቆሎ፣ ካሳቫ እና ስኳር ድንች በማልማት ነው። ዛምቢያ ውስጥ የሉንዳ ተናጋሪዎች የሚኖሩት ታዋቂ በሆነው በዛምቤዚ ወንዝ መነሻ አካባቢ ነው፤ ዛምቤዚ ወንዝ አፍሪካ ውስጥ በትልቅነቱ ከናይል፣ ከኮንጎ እና ከኒጀር ወንዞች ቀጥሎ አራተኛ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ለሉንዳ ተናጋሪዎች መስበክ የጀመሩት በ1930ዎቹ ሲሆን ጽሑፎችን ወደ ሉንዳ መተርጎም የጀመሩት ደግሞ በ2003 ነው።

መስከረም 2019 የሉንዳ የትርጉም ቡድን አዲስ ወደተገነባው የርቀት የትርጉም ቢሮ ተዛወረ። ቡድኑ ወደዚያ መዛወሩ አስተማማኝ የሆነ ኢንተርኔትና ሌሎች ነገሮች እንዲሟሉለት አድርጓል፤ ይህም ሥራውን ለማቀላጠፍ አስችሏል።

በቅርቡ የተገነባው በምዊኒሉንጋ፣ ዛምቢያ የሚገኘው የርቀት የትርጉም ቢሮ

ለበርካታ ዓመታት አስፋፊዎች የሚጠቀሙባቸው መጽሐፍ ቅዱሶች በጣም ውድና ለማግኘት አስቸጋሪ ከመሆናቸውም ሌላ የሚጠቀሙት ጥንታዊ ቋንቋ ነበር። በሉንዳ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም ግልጽና ለመረዳት ቀላል ነው። ለምሳሌ የቀድሞዎቹ የሉንዳ መጽሐፍ ቅዱሶች በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘውን “ዘር” የሚለውን ቃል የተረጎሙት በብዙ ቁጥር ነበር። በዚህም የተነሳ አስፋፊዎች ትንቢቱ በዋነኝነት የሚያመለክተው ኢየሱስን እንደሆነ ማስረዳት ከባድ ሆኖባቸው ነበር። በሉንዳ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም ግን ቃሉን በነጠላ ቁጥር አስቀምጦታል።

ተርጓሚዎቹ በአዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በጣም ተደስተዋል። አንደኛው ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ይህን ትርጉም ሲያነቡ ወደ ፈጣሪያቸው ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንደቀረቡ እንደሚሰማቸው እርግጠኛ ነኝ።”

አዲስ ዓለም ትርጉም በሉንዳ ቋንቋ መውጣቱ ይሖዋ በሁሉም ብሔራት ውስጥ ላሉ ሰዎች እንደሚያስብ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ሕዝቦች የመንግሥቱን መልእክት “እስከ ዓለም ዳርቻዎች” ለማሰማት በሚያደርጉት ጥረት ያግዛቸዋል።—ሮም 10:18