በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 10, 2023
ዛምቢያ

የማቴዎስ ወንጌል በዛምቢያ የምልክት ቋንቋ ወጣ

የማቴዎስ ወንጌል በዛምቢያ የምልክት ቋንቋ ወጣ

ሐምሌ 1, 2023 የማቴዎስ ወንጌል በዛምቢያ የምልክት ቋንቋ ወጣ፤ በሉሳካ፣ ዛምቢያ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ በተካሄደ ልዩ ፕሮግራም ላይ የመጽሐፉን መውጣት ያበሰረው የዛምቢያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኢየን ጄፈርሰን ነው። በፕሮግራሙ ላይ 922 ሰዎች ተገኝተዋል። በዚህ ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ሲወጣ ይህ የመጀመሪያው ነው። መጽሐፉን ከ​jw.org እና JW Library Sign Language ከተባለው አፕሊኬሽን ላይ ማውረድ ይቻላል።

ተርጓሚዎች ቅጂ ክፍል ውስጥ

በዛምቢያ የምልክት ቋንቋ የመጀመሪያው ጉባኤ የተቋቋመው መጋቢት 2008 ነው። በ2012 በሉሳካ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የትርጉም ቡድን ተቋቋመ። በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ በሚገኙ 16 የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎችና 11 ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ ወደ 500 የሚጠጉ አስፋፊዎች አሉ።

ወንድም ጄፈርሰን ይህ ትርጉም ለመረዳት ምን ያህል ቀላልና ግልጽ እንደሆነ ለማሳየት ማቴዎስ 18:22⁠ን በንግግሩ ላይ እንደ ምሳሌ ጠቅሷል። ይህ ጥቅስ በእንግሊዝኛው ትርጉም ላይ 18 ቃላትን የያዘ ነው። ጥቅሱ ወደ ዛምቢያ የምልክት ቋንቋ ቃል በቃል ቢተረጎም አንባቢዎቹ ለመረዳት ከባድ ይሆንባቸዋል። ሆኖም የጥቅሱ ሐሳብ በዛምቢያ የምልክት ቋንቋ የተገለጸው በሁለት ምልክቶች ብቻ ነው። ወንድም ጄፈርሰን እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያለ እጥር ምጥን ያለና ያልተወሳሰበ ትርጉም፣ ተመልካቾቹ ሐሳቡን መከታተልና መረዳት እንዲሁም ከአምላክ ቃል መጠቀም ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል።”

የማቴዎስ ወንጌል በዛምቢያ የምልክት ቋንቋ መዘጋጀቱ ይሖዋ ‘ሁሉም ዓይነት ሰዎች መዳን እንዲያገኙ’ እንደሚፈልግ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።—ቲቶ 2:11