በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሚያዝያ 12, 2021
ዛምቢያ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በማምብዌ ሉንጉ ቋንቋ ወጣ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በማምብዌ ሉንጉ ቋንቋ ወጣ

ሚያዝያ 3, 2021 በማምብዌ ሉንጉ ቋንቋ የተዘጋጀው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም የኤሌክትሮኒክ ቅጂ ወጣ። የዛምቢያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም አልበርት ሙሶንዳ አስቀድሞ በተቀዳ ፕሮግራም አማካኝነት ይህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደወጣ ያበሰረ ሲሆን በዛምቢያና በታንዛኒያ ያሉ አስፋፊዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። በዛምቢያ 2,531፣ በታንዛኒያ ደግሞ 325 አስፋፊዎች የማምብዌ ሉንጉ ቋንቋን ይናገራሉ፤ ቋንቋው በታንዛኒያ ፊፓ በሚለው መጠሪያም ይታወቃል።

ሦስት ተርጓሚዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን በዚህ ፕሮጀክት ላይ የተሳተፈ ሲሆን የትርጉም ሥራውን ለማጠናቀቅ 21 ወራት ፈጅቶባቸዋል። አንድ ተርጓሚ፣ የቋንቋው ተናጋሪዎች ቀደም ሲል ይጠቀሙበት የነበረው የማምብዌ ሉንጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የድሮ ቃላትን ስለሚጠቀም አንዳንዶች ለመረዳት ይቸገሩ እንደነበር ገልጿል። ሌላ ተርጓሚ ደግሞ በቅርቡ ስለወጣው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በሚጠቀሙበት ቋንቋ የተዘጋጀ ነው” ብሏል።

ከይሖዋ የተገኘው ይህ ግሩም ስጦታ በርካታ የማምብዌ ሉንጉ ተናጋሪዎች በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል በማንበብ ደስታ እንዲያገኙ እንደሚያስችል እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 1:2