ታኅሣሥ 7, 2020
ዩናይትድ ስቴትስ
ልጆች ወረርሽኙ ሳያግዳቸው በስብከቱ ሥራ በትጋት እየተካፈሉ ነው
ማይክ ኡዉቹኩ፣ ልጁ ሜሎዲ በኢንተርኔት አማካኝነት ከምትከታተለው ትምህርት ለምሳ እረፍት ተለቃ ደረጃውን ወደ ታች ስትወርድ ይሰማል። የስድስት ዓመት ልጁ እንዲህ በችኮላ ወርዳ ምን እያደረገች እንደሆነ ለማየት እሷ ወዳለችበት ይሄዳል፤ ሳንድዊች እየበላች ወይም በአሻንጉሊቶቿ እየተጫወተች እንደሚያገኛት ጠብቆ ነበር። ያየው ነገር ግን በጣም አስገረመው።
ማይክ እንዲህ ብሏል፦ “ላፕቶፕ ከፍታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ? የሚለውን መጽሐፍ አብረዋት ለሚማሩ ሦስት ልጆች እያሳየች ነበር። ሜሎዲ ‘አባዬ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እያስጠናኋቸው ነው!’ አለችኝ።”
ሜሎዲ በሂውስተን፣ ቴክሳስ የሚገኘው ትምህርት ቤቷ መስከረም 2020 ላይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በኢንተርኔት አማካኝነት ትምህርት መስጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር ቆርጣ ተነስታ ነበር። በመሆኑም ወደ ይሖዋ ጸልያ ጥናት የምታስጀምርበትን አጋጣሚ መፈለግ ጀመረች።
ማይክ እና እናቷ ኦክቴቪያ ልጃቸው ባደረገችው ነገር በጣም ተደሰቱ። ማይክ እንዲህ ብሏል፦ “ሜሎዲ አብረዋት ለሚማሩት ልጆች ሁልጊዜ ስለ ይሖዋ ትናገራለች። መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና ማየታችን ግን እኔም ሆንኩ እናቷ ልባችን በጥልቅ እንዲነካ አድርጓል።”
ሜሎዲ አብረዋት የሚማሩትን ልጆች መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናቷን ቀጥላለች። እንዲህ ብላለች፦ “እስካሁን ስለ ገነት እና ስለ ኢየሱስ አስተምሬያቸዋለሁ። የይሖዋ ምሥክር እንዲሆኑ እፈልጋለሁ!”
በኢንግልሳይድ፣ ኢሊኖይ የሚኖረው የዘጠኝ ዓመቱ ሳሙኤል ሞልናርም የሚያምንበትን ነገር ለሌሎች ይናገራል።
አንድ ወንድም በአጥር በኩል ለጎረቤቱ እንደሰበከ የሚገልጽ ተሞክሮ ሲሰማ እሱም እንዲህ ለማድረግ ወሰነ። የጎረቤታቸው የልጅ ልጅ በጓሮ በኩል ሲጫወት ሲያይ ልጁን ስለ ገነት መስማት ይፈልግ እንደሆነ ጠየቀው። መስማት እንደሚፈልግ ሲነግረው ሳሙኤል እየሮጠ ወደ ቤቱ ገብቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ይዞ ወጣ።
ሳሙኤል እንዲህ ብሏል፦ “ወደፊት ከእንስሳት ጋር ምንም ጉዳት ሳይደርስበት መጫወት እንደሚችል ነገርኩት። ከዚያም ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ እንደተጣለ የሚገልጸውን ታሪክ አነበብኩለት።”
ሳሙኤል በዚህ አላቆመም። jw.org ላይ ስላሉት የልጆች መልመጃዎችና ቪዲዮዎች የሚገልጽ ደብዳቤ ላከለት። ሁለቱ ልጆች ወደፊት ሲገናኙ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ለማንበብ ተስማሙ።
ሳሙኤል ባገኘው ተሞክሮ በጣም የተደሰተ ሲሆን ቀጣዩ ግቡ ላይ ለመድረስ ጠንክሮ እየሠራ ነው። “በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ ያሉትን ትራክቶች በሙሉ በደንብ ካወቅኩ በኋላ ሰዎችን ለማስተማር ልጠቀምባቸው እፈልጋለሁ” ብሏል።
በሂውስተን የሚኖሩ ሦስት ወጣት እህቶች በቅርቡ አንድ መንፈሳዊ ግባቸው ላይ መድረስ ችለዋል፤ ግባቸው ትምህርት ሲዘጋ ረዳት አቅኚ ሆኖ ማገልገል ነበር።
ነሐሴ ላይ የ13 ዓመቷ ጆስሊን ሆርታ፣ የ12 ዓመቷ ሜላኒ አልቫሬዝ እና የ10 ዓመቷ ክሎዊ ሮድሪጌዝ ደብዳቤ ለመጻፍ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተገናኙ። በሳምንት እስከ አምስት ጊዜ ድረስ በዚህ መልኩ ይገናኙ ነበር፤ አንዳንዴ የሚጀምሩት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ ነው።
ጆስሊን “አብረን እየተጫወትን እንበላና 1:30 ሲሆን ደብዳቤ መጻፍ እንጀምራለን” ብላለች። አልፎ አልፎ ከሦስቱ አንዳቸው ተኝተው የሚያረፍዱበት ጊዜ አለ፤ በዚህ ጊዜ የቀሩት ሁለቱ “ነግቷል! ተነሺ! አገልግሎት እንጀምር!” የሚል የጽሑፍ መልእክት ላረፈደችው ልጅ ይልካሉ።
የልጆቹ ቅንዓት እርስ በርስ እንዲበረታቱ ከማድረግ ባለፈ ሌሎች ጓደኞቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውንም አበረታቷል። የጆስሊን እናት አሊሺያ እንዲህ ብላለች፦ “በአገልግሎት ለመካፈል የምሰንፍበት ጊዜ አለ። ጆስሊን ቁጭ ብላ ስታገለግል ሳይ ግን ‘እኔም በስብከቱ ሥራ መካፈል እፈልጋለሁ!’ እላለሁ።”
ይሖዋ ወረርሽኝ በተከሰተበት በዚህ ወቅት በአገልግሎት ለመካፈል አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እያደረጉ ያሉ ታማኝ ወጣቶችን ሲያይ በጣም ይደሰታል።—ምሳሌ 27:11