ኅዳር 20, 2019
ዩናይትድ ስቴትስ
በካሊፎርኒያ ገጠራማ አካባቢዎች የተነሳው ሰደድ እሳት ከባድ ጉዳት አደረሰ
ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በካሊፎርኒያ ግዛት በተደጋጋሚ የተከሰተው ሰደድ እሳት 362 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ገደማ በሚሸፍን ቦታ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፤ ሰደድ እሳቱ በአካባቢው መልክዓ ምድር ላይ ጠባሳ ትቶ አልፏል።
የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ከ1,700 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ከእሳቱ ለመሸሽ ሲሉ አካባቢውን ለቀው ወጥተው እንደነበር ሪፖርት አድርጓል። ደስ የሚለው በሰደድ እሳቱ የተጎዳም ሆነ የሞተ ሰው የለም። ጥቅምት 10, 2019 በካሊሜሳ ባሉ የሰንደል ዛፎች ላይ የተነሳው እሳት የአንድ ወንድማችንን ቤት አውድሟል። በተጨማሪም ጭሱ በአንዳንድ ቤቶች ላይ መጠነኛ ጉዳት አድርሷል። አካባቢያውን ለቅቀው የወጡት ሰዎች በሙሉ ማለት ይቻላል ወደ መኖሪያቸው ተመልሰዋል።
ጉዳት በደረሰበት አካባቢ የሚኖር አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ ወቅት መመሪያዎችን መከተል በጣም አስፈላጊ ነው። ወንድሞች አደጋ ያጠላባቸውን አካባቢዎች በፍጥነት ለቅቀው ወጥተዋል፤ ይህም የእሳት አደጋ ሠራተኞች ትኩረታቸውን ሰዎችን በመፈለግ ላይ ሳይሆን እሳቱን በማጥፋት ላይ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል።”
የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማሌዎች ከአካባቢያቸው ሸሽተው ለነበሩ ወንድሞች የሚደረገውን የእርዳታ ሥራ ማስተባበራቸውን ቀጥለዋል። በአጎራባች አካባቢ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ያሳዩት ፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አስደናቂ ነው። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በዚያ ወቅት የታየውን ግሩም ክርስቲያናዊ ፍቅር ሲገልጽ “ለተፈናቀሉት በሙሉ ማረፊያ ለማግኘት አልተቸገርንም ነበር” ብሏል።
እነዚህ ክርስቲያኖች በሰደድ እሳቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞችና እህቶች “የብርታት ምንጭ” በመሆናቸው ይሖዋን እናመሰግናለን።—ቆላስይስ 4:11