ሚያዝያ 28, 2021
ዩናይትድ ስቴትስ
በካሪቢያን በተከሰተ እሳተ ገሞራ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቀሉ
ቦታ
በሴንት ቪንሰንት እና በባርባዶስ ያሉ የተወሰኑ አካባቢዎች
የደረሰው አደጋ
ሚያዝያ 9, 2021 ላ ሱፍሪዬር የተባለው እሳተ ገሞራ አመድና ጭስ መትፋት ጀመረ
ከፍተኛ መጠን ያለው አመድ በሕንፃዎች ላይ ጉዳት ያስከተለ ከመሆኑም ሌላ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ምክንያት ሆኗል፤ በዚህም የተነሳ በአካባቢው የመጠጥ ውኃ እጥረት ተከስቷል
እሳተ ገሞራው ለሳምንታት ያህል ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
በሴንት ቪንሰንት እና በባርባዶስ ያሉ 185 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል
በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት
ባለሥልጣናት በሴንት ቪንሰንት ሰሜናዊ ክልል ወዳለው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት አካባቢ አሁንም ድረስ መግባት ስላልቻሉ የጉዳቱን መጠን በትክክል ማወቅ አልተቻለም
የእርዳታ እንቅስቃሴ
በሴንት ቪንሰንት እና በአቅራቢያዋ ባሉ አደጋ ያልደረሰባቸው ደሴቶች የሚኖሩ አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትን ወንድሞችና እህቶች ቤታቸው ተቀብለዋቸዋል፤ ይህን እያደረጉ ያሉት ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የወጡትን የደህንነት ደንቦች ሳይጥሱ ነው
በአካባቢው የሚሠራው የኮቪድ-19 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ፣ የእርዳታ ሥራውን እንዲያስተባብር ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ኮሚቴው ከወረዳ የበላይ ተመልካቾችና በአካባቢው ካሉ የጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር የመጠጥ ውኃ እያቀረበ ነው፤ በተጨማሪም አደጋ በደረሰባቸው አካባቢ የሚኖሩ ወንድሞችን ከአካባቢው በማስወጣቱ ሥራ እገዛ እያደረገ ነው
በሴንት ቪንሰንት እና በሴንት ሉሺያ ያሉ ባለሥልጣናትም በአደጋው ለተጎዱት እርዳታ አበርክተዋል
አደጋው በደረሰበት አካባቢ ብቻቸውን የሚኖሩ አንድ በዕድሜ የገፉና ዓይነ ስውር የሆኑ ወንድም፣ ልክ እሳተ ገሞራው ከመፈንዳቱ በፊት በወንድሞች እርዳታ አካባቢውን ለቀው መውጣት ችለዋል። ወንድሞች ከአደጋ ነፃ ወደሆነው አካባቢ ሲሄዱ በርካታ ሰዎች ከአደጋው ለመሸሽ በሚያደርጉት ጥረት በመንገዱ ላይ ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሮ ነበር። ደስ የሚለው ሁሉም አስፋፊዎች በሰላም አካባቢውን ለቀው መውጣት ችለዋል።
የእርዳታ ሥራው ወንድሞቻችን መጠጊያና መጽናኛ እንዲያገኙ ስላስቻላቸው ደስተኞች ነን። በሥራው የተካፈሉት ወንድሞች “በጭንቅ ጊዜ ፈጥኖ የሚደርስልን ረዳታችን” የሆነውን አምላካችንን እንደሚመስሉ አሳይተዋል።—መዝሙር 46:1-3