መጋቢት 11, 2021
ዩናይትድ ስቴትስ
በደብዳቤ የሚሰጥ ምሥክርነት የሚያበረታታ ውጤት ማስገኘቱን ቀጥሏል
በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በደብዳቤ አማካኝነት መመሥከር አስደሳች ሆኖላቸዋል። ከዩናይትድ ስቴትስ የተገኙት የሚከተሉት ተሞክሮዎች ይህ ዘዴ የመጽሐፍ ቅዱስን አጽናኝ መልእክት በማስፋፋት ረገድ ውጤታማ እንደሆነ ያሳያሉ።
በብሉ አሽ፣ ኦሃዮ የምትኖር ካርሊ ረግልስ የተባለች የ13 ዓመት እህታችን፣ የላከችው ደብዳቤ ያልተጠበቀ ምላሽ ማስገኘቱ በደብዳቤ አማካኝነት መመሥከር ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ አስገንዝቧታል።
አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ካርሊ የቤታቸው ደጃፍ ላይ እያለች አንድ ሰው በሞተር ብስክሌት ወደ ቤታቸው መጣ። ሰውየው ከሞተር ብስክሌቱ ወርዶ አንድ ፖስታ በእጁ እያውለበለበ “ይሄን ደብዳቤ የላከልኝ ማን ነው?” በማለት ጮኸ። ካርሊ ይህ ደብዳቤ በአገልግሎት ስትካፈል የላከችው እንደሆነ አስታወሰች።
የካርሊ ወላጆች ይህን ሲያዩ ቶሎ ብለው ወደ ደጅ ወጡ፤ ካርሊም “ደብዳቤውን የላክሁት እኔ ነኝ” በማለት በድፍረት መለሰች።
ከዚያም ሰውየው “ደብዳቤውን የላክሽው ልክ በሚያስፈልገኝ ጊዜ ነው!” ሲል ካርሊ እና ወላጆቿ ተገረሙ። ሰውየው አክሎም በወረርሽኙ ምክንያት ብቸኝነት ተሰምቶት በነበረ ወቅት ደብዳቤው እንዳጽናናው ተናገረ። በተጨማሪም በቅርቡ ወንድሙን በሞት እንዳጣ እና የካርሊ ደብዳቤ ከሐዘኑ እንዲጽናና እንደረዳው ገለጸ።
በመጨረሻም እንዲህ አለ፦ “ለሰዎች ደብዳቤ መጻፋችሁን አታቁሙ። ሰዎቹ ለደብዳቤያችሁ ምላሽ ሰጡም አልሰጡ ደብዳቤያችሁ የሰዎችን ልብ ይነካል።”
ካርሊ ለጎረቤቶቿ ደብዳቤ መጻፏን ለመቀጠል ይበልጥ ተነሳስታለች። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ አንድን ሰው ለማበረታታት ስለተጠቀመብኝ በጣም ደስተኛ ነኝ። የምንጽፈው ደብዳቤ በእርግጥም የሰዎችን ልብ ሊነካ ይችላል።”
በሴንተር፣ ቴክሳስ የምትኖረው እህት ሚርና ሎፔዝ፣ የምትልካቸው ደብዳቤዎች ቅን ልብ ወዳላቸው ሰዎች እየደረሱ መሆኑን መጠራጠር ጀምራ ነበር፤ በዚህ ወቅት አንድ አስገራሚ ነገር አጋጠማት። ሚርና አንድ ዘመዷ እስር ቤት እንደገባ ሰማች። ይህ ወጣት በልጅነቱ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ ነበር። ሚርና ለዚህ ወጣት ደብዳቤ በመጻፍ ይሖዋ እንዳልረሳው ገለጸችለት።
የሚርና ዘመድ ለደብዳቤዋ ምላሽ ሰጠ። ከታሰረ በኋላ በጭንቀትና በተስፋ መቁረጥ እንደተዋጠ ገለጸ። እስር ቤት መግባቱ የልጅነት ሕይወቱን እንዲያስታውስና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እንዲሁም ወደ ይሖዋ መጸለይ እንዲጀምር እንዳነሳሳው ተናገረ። የሚርና ደብዳቤ የጸሎቱ መልስ እንደሆነ የገለጸ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ አሁንም እንደሚያስብለት የሚያሳይ ማስረጃ አድርጎ እንደተመለከተው ጽፏል።
በኖርክሮስ፣ ጆርጂያ የምትኖረው እህት ናታሊ ቢብዝ ከአንዲት ሴት መልእክት ደረሳት፤ ሴትየዋ ስፖርት እየሠራች እያለ የናታሊን ደብዳቤ አግኝታ ነበር። ሴትየዋ ደብዳቤውን መንገድ ላይ ወድቆ ብታየውም መጀመሪያ ላይ ትታው ሩጫዋን ቀጠለች። ሆኖም ለምን እንደሆነ ባይገባትም ተመልሳ ደብዳቤውን ለማንሳት ወሰነች።
ሴትየዋ ለናታሊ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “ያ ሳምንት በጣም ከባድ ነበር፤ ስለዚህ አንድ ጥሩ ነገር ለማግኘት ተመኝቼ ነበር። የአንቺ ደብዳቤ ሲደርሰኝ የተመኘሁትን ‘ጥሩ ነገር’ አገኘሁ!”
ናታሊ እንዲህ ብላለች፦ “ይህን ምላሽ ማግኘቴ በየትኛውም የአገልግሎት ዘርፍ ብንካፈል ይሖዋ ጥረታችንን እንደሚባርክልን እንድተማመን አድርጎኛል።”
በአቴንስ፣ ቴክሳስ የምትኖረው እህት ሎራ ማርቲኔዝ፣ አስቤዛ ለመግዛት ስትወጣ ዕቃዋን ወደ መኪናዋ ለሚያመጡላት ሠራተኞች ደብዳቤ ትሰጣቸዋለች። ከሠራተኞቹ መካከል አንዷ ደብዳቤው ልቧን በጥልቅ እንደነካው ለሎራ ነገረቻት። ሎራም ለዚህች ሴት ሌሎች ሁለት ደብዳቤዎች ሰጠቻት፤ በአሁኑ ወቅት ይህችን ሴት መጽሐፍ ቅዱስ እያስጠናቻት ነው።
እንዲህ ያሉት ተሞክሮዎች፣ የምንዘራቸው የእውነት ዘሮች የት ‘እንደሚያድጉ’ ባናውቅም ይሖዋ በእያንዳንዱ የአገልግሎት ዘርፍ ተጠቅመን የምናከናውነውን ሥራ በግ መሰል ለሆኑ ሰዎች ማጽናኛና ተስፋ ለመስጠት እንደሚጠቀምበት ያሳያሉ።—መክብብ 11:6