በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በፓተርሰን ቤቴል የሚገኘው አዲሱ የጎብኚዎች ማዕከል ግንባታ

የካቲት 10, 2022
ዩናይትድ ስቴትስ

በፓተርሰን ቤቴል እየተከናወነ ያለው የእድሳትና የግንባታ ሥራ

በፓተርሰን ቤቴል እየተከናወነ ያለው የእድሳትና የግንባታ ሥራ

ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል ውስጥ እየተገነባ ያለውና 2,787 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ባለ ሁለት ወለል የጎብኚዎች ማዕከል በ2023 አጋማሽ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ሕንፃው አንድ ቤተ መዘክር፣ ሦስት ቋሚ ጋለሪዎችና አንድ ተንቀሳቃሽ ጋለሪ ይኖረዋል፤ እንዲሁም በቀን 1,200 ጎብኚዎችን ማስተናገድ ይችላል። በተጨማሪም በማዕከሉ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ሕንፃዎች እድሳት እየተደረገላቸው ሲሆን ያረጁ የኤሌክትሪክ፣ የውኃና የፍሳሽ መስመሮች በአዲስ እየተቀየሩ ነው። ከእድሳትና ከግንባታ ሥራው 40 በመቶ ገደማ የሚሆነው ተጠናቅቋል።

ፕሮጀክቱን እያስተባበሩ ያሉት ወንድሞች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ የተለያዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የግንባታ ቁሳቁሶች አቅርቦት እጥረት በመከሰቱ ሥራውን መቀጠል ከባድ ሆኖ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ወሳኝ በሆነ የግንባታው ወቅት ላይ ኮንክሪት ለመሥራት የሚያስችል በቂ የሲሚንቶ አቅርቦት አልነበረም፤ ሆኖም ወንድሞች የወለሉን አብዛኛውን ክፍል የሚሸፍን ኮንክሪት መሥሪያ ሲሚንቶ በማግኘታቸው በታቀደው ጊዜ ሥራቸውን ማከናወን ችለዋል። ከዚህም ሌላ የብረት ዋጋ በጣም ንሮ የነበረ ቢሆንም ወንድሞች የሚያስፈልጋቸውን ያህል ብረት በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት ችለዋል፤ ይህ የሆነው አስቀድመው ኮንትራቶችን ተዋውለው ስለነበረ ነው።

ቤቴል ተዘግቶ በነበረበት ጊዜ ደግሞ ፈቃደኛ ሠራተኞች በርቀት ከየቤታቸው ሆነው ይሠሩ ስለነበር የዕቅድና የንድፍ ሥራዎቹ አልዘገዩም። እርግጥ ነው፣ በወረርሽኙ ምክንያት በተጣሉት ገደቦች የተነሳ ለተወሰነ ጊዜ ያህል የከተማዋን ባለሥልጣናት ማግኘት አልተቻለም ነበር፤ ይህም ሥራውን ሊያጓትተው ይችል ነበር። ያም ቢሆን የግንባታ ኮሚቴው ከተለያዩ የቤቴል ዲፓርትመንቶችና ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር ተቀራርቦ ይሠራ ነበር፤ በተጨማሪም የርቀት ፈቃደኛ ሠራተኞችንና የቪዲዮ ኮንፍረንስ በመጠቀም ለግንባታው የሚያስፈልጉ ፈቃዶችን በተገቢው ጊዜ ማግኘት ተችሏል።

ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የሚጣሉት ገደቦች በየጊዜው ስለሚቀያየሩ አዳዲስ ፈቃደኛ ሠራተኞችን ወደ ግንባታ ቦታው መጋበዝ አልተቻለም ነበር፤ ይህ ደግሞ ሌላ ተፈታታኝ ሁኔታ ፈጥሯል። ያም ቢሆን በመስከረም 2020 አካባቢ በግንባታ ቦታው እየኖሩ የሚሠሩ አዳዲስ ፈቃደኛ ሠራተኞችን እንደገና መጋበዝ ተቻለ።

እህት ጄኔፈር ፖል በፕሮጀክቱ ላይ እንድትካፈል የተጋበዘችው በወረርሽኙ ወቅት ነበር። ስለ ግንባታ ሥራው ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ከባድ ሥራ እወዳለሁ። ሆኖም የምወደው ሥራውን ብቻ ሳይሆን ሰዎቹንም ነው። የይሖዋን መመሪያ በግልጽ ተመልክቻለሁ፤ እንዲሁም ድርጅቱ የሚያከናውነውን ሥራ ማየት ችያለሁ።”

በአሁኑ ጊዜ በግንባታው ቦታ ላይ ያሉትን 350 ገደማ የሚሆኑ ሠራተኞች ጨምሮ በድምሩ 440 ፈቃደኛ ሠራተኞች በፓተርሰን የጎብኚዎች ማዕከል ግንባታና በእድሳት ፕሮጀክቶች ላይ እየተካፈሉ ነው። ይሖዋ ፕሮጀክቱ ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስፈልገውን ሁሉ እያሟላ እንደሆነ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እየተመለከቱ ነው።—1 ዜና መዋዕል 29:16

 

ወንድሞች ለፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ የሚሆን ጉድጓድ እየቆፈሩ

አንዲት እህት የጥገና ክፍሉ ሕንፃ ሲታደስ የማሞቂያና የማቀዝቀዣ መሣሪያዎቹን የኤሌክትሪክ መስመር እየዘረጋች

አንድ ወንድም በክሬን ተጠቅሞ የብረት ምሰሶ ሲያነሳ

አዲሱ የጎብኚዎች ማዕከልና ከበስተ ጀርባው ያለው የትምህርት ማዕከል ከላይ ሲታዩ

በጎብኚዎች ማዕከሉ ሁለተኛ ፎቅ ላይ አንድ ወንድም ለሕንፃው ድጋፍ ሆኖ የሚያገለግለውን ብረት እየሞረደ

አዲሱ የማሞቂያና የማቀዝቀዣ መሣሪያ፣ የቢሮ ሕንፃው ጣሪያ ላይ በክሬን እየተሰቀለ

በግንባታ ሥራው ላይ በደስታ የሚካፈሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች

የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች በምሽቱ ክፍለ ጊዜ በጉብኝት ማዕከሉ ፎቅ ላይ እየሠሩ