ሰኔ 13, 2019
ዩናይትድ ስቴትስ
ኃይለኛ ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ በተወሰኑ የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ላይ ከባድ ጉዳት አደረሰ
ግንቦት 2019 ላይ በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ግዛቶች የጣለው ከባድ ዝናብና በእነዚያ አካባቢዎች የተከሰቱት 500 ገደማ የሚሆኑ ቶርኔዶዎች (ኃይለኛ አውሎ ነፋሳት) ከባድ ጉዳት እንዳደረሱ አንዳንድ የዜና ዘገባዎች ጠቁመዋል።
በአርከንሶ፣ በኢንዲያና፣ በሚሲሲፒ፣ በሚዙሪ፣ በኦሃዮ፣ በኦክላሆማ፣ በፔንስልቬንያና በቴክሳስ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ አስቸጋሪ የአየር ጠባይ የተነሳ ጉዳት ደርሶባቸዋል። እርግጥ በዚህ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ወንድሞችም ሆኑ እህቶች የሉም። ሆኖም በስድስት የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን አራቱ ሆስፒታል ገብተው ነበር። በተጨማሪም 6 የወንድሞች ቤቶች ሙሉ በሙሉ የወደሙ ከመሆኑም ሌላ 98 ቤቶችና 12 የስብሰባ አዳራሾች ጉዳት ደርሶባቸዋል። በዚህ የተነሳ 84 የይሖዋ ምሥክሮች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
ወንድሞች የደረሰውን ጉዳት መጠን እያጣሩ ከመሆኑም በላይ የአደጋው ሰለባዎች ምግብ፣ ውሃና መጠለያ እንዲያገኙ ዝግጅት አድርገዋል። በአካባቢው ያሉ ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እያጽናኑና እያበረታቱ ነው።
ወንድሞቻችን አደጋው ካደረሰባቸው ጉዳት ለማገገም ጥረት ሲያደርጉ አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠታችንንና ለእነሱ መጸለያችንን እንቀጥላለን።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4