በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ እህት ሜሪ ላሪመር ከመጀመሪያው የጊልያድ ክፍል ሌሎች ተማሪዎች ጋር፤ እህት ሜሪ ሰኔ 23, 1943 የተሰጣቸው ዲፕሎማ፤ እህት ሜሪ በ2017

ጥር 23, 2024
ዩናይትድ ስቴትስ

ከመጀመሪያው የጊልያድ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች የመጨረሻዋ በ103 ዓመታቸው አረፉ

ከመጀመሪያው የጊልያድ ትምህርት ቤት ተመራቂዎች የመጨረሻዋ በ103 ዓመታቸው አረፉ

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ የመጀመሪያው ክፍል ተመራቂ የሆኑት ሜሪ ላሪመር ኅዳር 23, 2023 በሞት አንቀላፍተዋል። a እህት ሜሪ የተወለዱት ሰኔ 4, 1920 በሲነሪ ሂል፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነው። በ1935 በ15 ዓመታቸው በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተጠመቁ። ከአራት ዓመት በኋላ እህት ሜሪ በዘወትር አቅኚነት ማገልገል የጀመሩ ሲሆን በታታሪነታቸው ይታወቁ ነበር።

ታኅሣሥ 1942 እህት ሜሪ በወቅቱ በድርጅቱ ውስጥ አመራር ይሰጥ ከነበረው ከወንድም ናታን ኖር አንድ ደብዳቤ ደረሳቸው፤ ደብዳቤው አዲስ በተከፈተው ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ለመማር እንዲያመለክቱ የሚጋብዝ ነበር። ግብዣው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “የኮሌጁ ዓላማ ራሳቸውን [ለይሖዋ] የወሰኑ ወንዶችና ሴቶች በመላው ዓለም ሚስዮናውያን ሆነው እንዲያገለግሉ ማሠልጠን ነው። . . . በኮሌጁ ውስጥ ለአምስት ወራት የሚዘልቅ ሥልጠና ይሰጣል። . . . በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግና በትጋት ማጥናት ያስፈልጋል።” እህት ሜሪ ወዲያውኑ ማመልከቻውን ሞልተው ላኩ።

የካቲት 1, 1943 እህት ሜሪና ሌሎች 99 ተማሪዎች በሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ትምህርታቸውን ጀመሩ። አምስት ወር ገደማ በፈጀው ሥልጠና ላይ እህት ሜሪ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ይበልጥ ለመማር ትጋት የተሞላበት ጥረት አድርገዋል። ጎበዝ ተማሪ የነበሩ ሲሆን ሰኔ 23, 1943 ተመረቁ።

እህት ሜሪና ሌሎች ተማሪዎች በጊልያድ ትምህርት ቤት መግቢያ አናት ላይ ከሚገኝ ሰገነት ላይ ሆነው እጃቸውን እያውለበለቡ (ሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ)

ከዚያም በኩባ ተመድበው በሚስዮናዊነት ማገልገል ጀመሩ። አዲሱ ምድብ ላይ ካጋጠሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች አንዳንዶቹን ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “በዚያ ያሉት ሰዎች ድሆች ነበሩ። አገልግሎታችንን ስናከናውን በእግራችን መጓዝ ነበረብን . . . መኪና አልነበረንም።” እህት ሜሪ፣ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን እናታቸውን ለመንከባከብ ወደ ፔንስልቬንያ መመለስ ስለነበረባቸው በሚስዮናዊ ምድባቸው ላይ የቆዩት እስከ 1948 ነው። በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት እህት ሜሪ በአገልግሎትና በሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች የተሟላ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ እህት ሜሪ አላገቡም። በሞት ባንቀላፉበት ወቅት በግሌንዴል፣ ካሊፎርኒያ በሚገኝ ጉባኤ ውስጥ እያገለገሉ ነበር።

እህት ሜሪ በኩባ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ሲካፈሉ

እህት ሜሪ (በስተ ግራ) ከእህታቸው ከሔለን ፌራሪና ከባለቤቷ ከሳልቪኖ ጋር። ሔለንና ሳልቪኖ በሁለተኛው የጊልያድ ክፍል ሠልጥነው በኩባ አገልግለዋል

ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በአሁኑ ወቅት የሚገኘው በፓተርሰን ኒው ዮርክ ሲሆን የ155ኛው ክፍል ተማሪዎች እየተማሩ ነው። የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ማርክ ኑሜር እህት ሜሪ ማረፋቸውን ሲሰማ እንዲህ አለ፦ “ሜሪ ላሪመር ከትንሽ ከተማ የመጣችና ለሰዎች ስለ ይሖዋ ለመናገር ወደማታውቀው ቦታ ለመሄድ ፈቃደኛ የሆነች ወጣት ነበረች። ወዴት እንደምትላክም ሆነ መቼ እንደምትመለስ የምታውቀው ነገር አልነበረም። እንደ ሜሪ ያሉ የጊልያድ ሚስዮናውያን ዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ እንዲስፋፋ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።”​—ኢሳይያስ 6:8

a የመጠበቂያ ግንብ ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ከ1946 ወዲህ የመጠበቂያ ግንብ ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ተብሏል።