ሚያዝያ 23, 2020
ዩናይትድ ስቴትስ
ከ100 የሚበልጡ አውሎ ነፋሶች በደቡብ ምሥራቃዊ ዩናይትድ ስቴትስ ላይ ጉዳት አደረሱ
ከሚያዝያ 12 እስከ ሚያዝያ 13, 2020 ከ100 የሚበልጡ ዝናብ የቀላቀሉ አውሎ ነፋሶች በደቡብ ምሥራቃዊ ዩናይትድ ስቴትስ ላይ ጉዳት አድርሰዋል። የአገሪቱ ብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት እንደገለጸው አንደኛው አውሎ ነፋስ ሦስት ኪሎ ሜትር ገደማ የሚያክል ስፋት ነበረው፤ በመሆኑም በታሪክ ዘመናት ከተመዘገቡት ትላልቅ አውሎ ነፋሶች አንዱ ነው።
ቅርንጫፍ ቢሮው ወዲያውኑ በአካባቢው የሚያገለግሉ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን በማነጋገር ስለ ወንድሞችና እህቶች ደህንነት አጣርቷል። በአውሎ ነፋሱ ምክንያት ሕይወቱን ያጣ አንድም የይሖዋ ምሥክር የለም። አንዲት እህት አውሎ ነፋሱ ቤቷን በመምታቱ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባታል። በድምሩ 63 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፣ 12 ቤቶች ወድመዋል፣ 58 ቤቶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተጨማሪም አምስት የስብሰባ አዳራሾች መለስተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ አንድ የስብሰባ አዳራሽ ደግሞ ዛፍ ወድቆበት ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።
የጉባኤ ሽማግሌዎችና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሁኔታውን ማጣራታቸውን ቀጥለዋል። በተጨማሪም የወንድሞችንና የእህቶችን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸውን አስፋፊዎች ለማጽናናት ጥረት እያደረጉ ነው።—ኢሳይያስ 40:1