በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥር 13, 2020
ዩናይትድ ስቴትስ

ወቅታዊ መረጃ፦ ዶሪያን የተባለው አውሎ ነፋስ ከደረሰ በኋላ የተከናወነ የእርዳታ ሥራ

በአየር እና በባሕር የቀረበ እርዳታ

ወቅታዊ መረጃ፦ ዶሪያን የተባለው አውሎ ነፋስ ከደረሰ በኋላ የተከናወነ የእርዳታ ሥራ

ከመስከረም 1 እስከ መስከረም 3, 2019 ባለው ጊዜ በባሃማስ የደረሰው ዶሪያን የተባለው አውሎ ነፋስ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። አውሎ ነፋሱ ከመድረሱ በፊት የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ የእርዳታ ሥራውን ከፍሎሪዳ ግዛት ሲያስተባብር ቆይቷል። ወደ አካባቢው መጓዝ እንደተቻለ አውሮፕላንና ጀልባ ያላቸው ወንድሞች ፈጥነው ወደ ደሴቲቱ ደረሱ፤ ወንድሞቻችን በደሴቲቱ እርዳታ ለመስጠት ከመጡት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች መካከል ነበሩ።

አሥራ ሦስት ወንድሞችና እህቶች ከ300 በላይ የሆኑ በረራዎችን በማካሄድ 15 ቶን የሚመዝኑ የእርዳታ ቁሳቁሶችንና ከ700 የሚበልጡ የበጎ ፈቃድ ሠራተኞችን ጉዳት ወደደረሰበት አካባቢ አጓጉዘዋል። ከዚህም በተጨማሪ የወንድሞቻችን የግል ንብረት የሆኑ 13 ጀልባዎች ወደ 90 ቶን የሚጠጋ የእርዳታ ቁሳቁስ አድርሰዋል። ከፍሎሪዳ ባሃማስ በጀልባ የተደረገው የደርሶ መልስ ጉዞ በአማካይ 12 ሰዓት ወስዷል።

በፓልም ቢች ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ የበረራ ተቆጣጣሪ ሆኖ የሚሠራው ሆዜ ካብሬራ እንዲህ ብሏል፦ “ልክ አውሎ ነፋሱ እንዳቆመ፣ አስፈላጊ የእርዳታ ቁሳቁሶችን የያዙት [የይሖዋ ምሥክሮቹ] አውሮፕላኖች ጉዞ ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች ከሚጠበቅባቸው በላይ በማድረግ ረገድ ግሩም ምሳሌ ናቸው።”

ራሳቸውን በፈቃደኝነት ካቀረቡት አውሮፕላን አብራሪዎች አንዱ የሆነው ወንድም ግሌን ሳንደርስ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙዎቻችን በሙያችን ተጠቅመን ወንድሞቻችንን የመርዳት አጋጣሚ ስናገኝ ይህ የመጀመሪያችን ነው። ሥቃይ ለደረሰበት የአካል ክፍል እርዳታ የምናደርግ አነስተኛ ወይም ትንሽ የአካል ክፍል መሆናችን ከፍተኛ እርካታ አስገኝቶልናል።”—1 ቆሮንቶስ 12:26

የእርዳታ ሥራው 1,750,000 የአሜሪካ ዶላር ገደማ እንደሚወስድና ግንቦት 1, 2020 ድረስ እንደሚቀጥል የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ገልጿል።

 

በፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የእርዳታ ቁሳቁሶች ጀልባ ላይ ሲጫኑ። ወንድሞቻችን በድምሩ 29 ጉዞ ወደ ባሃማስ አድርገዋል

በውኃ የተጥለቀለቀው የግሬት አባኮ፣ ባሃማስ አውሮፕላን ማረፊያ

በበረራ ወቅት ከአብራሪዎቹ ክፍል ያለው እይታ