ጥቅምት 1, 2021
ዩናይትድ ስቴትስ
የማቴዎስ መጽሐፍ በህሞንግ ቋንቋ ወጣ
መስከረም 25, 2021 መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በህሞንግ ቋንቋ በዲጂታል ፎርማት ወጣ። መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን ያበሰረው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን ሲሆን በኢንተርኔት አማካኝነት የተካሄደውን ልዩ ስብሰባ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከ2,500 የሚበልጡ ሰዎች ተከታትለዋል።
ከአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በህሞንግ ቋንቋ የወጣው የመጀመሪያው መጽሐፍ ይሄ ነው። በመላው ዓለም ህሞንግ ቋንቋ የሚናገሩ ከ3.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አሉ። a የህሞንግ ሕዝቦች ተፈጥሮን ያመልካሉ፤ እንዲሁም በጥሩና በክፉ መናፍስት ኃይል ያምናሉ።
በ1970ዎቹ ዓመታት ብዙዎቹ የህሞንግ ሕዝቦች በታይላንድ ወደሚገኙ የስደተኛ መጠለያዎች ተሰደዱ። ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ ስደተኞች አንዳንዶቹ በምዕራባውያን አገሮች ውስጥ መኖር ጀመሩ፤ ብዙዎቹ የሄዱት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ነው።
በዛሬው ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የህሞንግ ሕዝቦች በአብዛኛው የሚኖሩት በካሊፎርኒያ፣ በሚኒሶታ እና በዊስኮንሰን ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎቻቸውን ወደ ህሞንግ መተርጎም የጀመሩት በ2007 ነው። በ2012 በሳክራሜንቶ፣ ካሊፎርኒያ የርቀት የትርጉም ቢሮ ተገነባ።
የትርጉም ቡድኑ የማቴዎስ መጽሐፍን ተርጉሞ ያጠናቀቀው በሦስት ወራት ውስጥ ነው። በአምስት የተለያዩ አገሮች የሚኖሩ አስፋፊዎች ትርጉሙን በመገምገም በሥራው ተካፍለዋል።
የትርጉም ቡድኑ በዚህ ፕሮጀክት ሲካፈል ለየት ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሞታል። ህሞንግ ቋንቋ በጽሑፍ መስፈር የጀመረው ከ1950ዎቹ ወዲህ ስለሆነ ወጥ የሆነ የፊደል አጻጻፍ ሥርዓት የለውም።
በህሞንግ ቋንቋ የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ከ1980ዎቹ አንስቶ የወጡ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱሶቹ በጣም ውድ በመሆናቸው የተነሳ ብዙዎቹ የህሞንግ ተናጋሪዎች ሊያገኟቸው አይችሉም ነበር። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱሶቹ በርካታ የትርጉም ስህተቶች አሏቸው፤ ይህም የቅዱሳን መጻሕፍትን መልእክት በትክክል መረዳት አዳጋች እንዲሆን አድርጓል። ለምሳሌ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም በአንድ ጥንታዊ የህሞንግ ተረት ውስጥ በሚገኝ ገጸ ባሕርይ ስም ተክቶታል።
አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “አሁን አዲስ ዓለም ትርጉም በህሞንግ ቋንቋ ስለወጣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የይሖዋን ስም በራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማንበብና የእሱ ወዳጅ መሆን ይችላሉ። ይህ ለበርካታ ዓመታት ስንጠብቀውና ስንጸልይበት የቆየነው ጉዳይ ነው።”
አንባቢዎች ግሩም የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በማግኘታቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል። አንድ አንባቢ እንዲህ ብሏል፦ “የማቴዎስ መጽሐፍን በህሞንግ ቋንቋ ሳነብ በጣም ተገረምኩ። ‘ይህ ትርጉም በውስጤ የተለያዩ ስሜቶችን ሊጭርብኝ የቻለው እንዴት ነው?’ ብዬ አሰብኩ። ታሪኩ ወዲያውኑ እውን ሆነልኝ።”
የማቴዎስ መጽሐፍ በህሞንግ ቋንቋ መውጣቱ፣ የማያዳላው አምላካችን እሱን የሚፈልጉት ሰዎች በሙሉ ቃሉን እንዲያገኙ እንደሚያደርግ የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35
a ተመራማሪዎች የህሞንግ ሕዝቦችን ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ ከባድ ሆኖባቸዋል። በቻይና ደቡባዊ ግዛቶች ውስጥ 2.7 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ የህሞንግ ሕዝቦች እንደሚኖሩ ይገመታል። በሰሜናዊ ቬትናም፣ በላኦስ፣ በታይላንድና በምሥራቅ ምያንማር 1.2 ሚሊዮን ገደማ የህሞንግ ሕዝቦች ይኖራሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ከ170,000 የሚበልጡ የህሞንግ ሕዝቦች ይኖራሉ።