ጥቅምት 6, 2022
ዩናይትድ ስቴትስ
የሴዳር ፖይንት ስብሰባ 100 ዓመት አስቆጠረ
ይህን ወሳኝ ክንውን የሚዘክር አዲስ ሙዚየም ተከፈተ
በዘመናችን የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ ከሆኑ ክንውኖች አንዱ በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደው ስብሰባ ነው፤ ከመስከረም 5-13, 1922 የተካሄደው ይህ የዘጠኝ ቀን ስብሰባ ዘንድሮ 100 ዓመት ሆኖታል። በስብሰባው ላይ የዩናይትድ ስቴትስ፣ የካናዳና የአውሮፓ ልዑካን ተገኝተው ነበር። በየቀኑ በአማካይ 10,000 ተሰብሳቢዎች ነበሩ፤ ንግግሮቹም በተመሳሳይ ጊዜ ላይ በ11 ቋንቋዎች ተላልፈዋል።
ይህን ታሪካዊ ስብሰባ የሚዘክርና በስብከቱ ሥራ ላይ ያመጣውን ትልቅ ለውጥ የሚያሳይ አዲስ ሙዚየም በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ተከፍቷል። በአሁኑ ወቅት ሙዚየሙን መጎብኘት የሚችሉት የቤቴል ቤተሰብ አባላት ብቻ ናቸው፤ የቤቴል ጉብኝት ሲጀመር ግን ለሕዝብ ክፍት ይሆናል።
የስብሰባው ጉልህ ክንውን የተስተናገደው መስከረም 8 ነው። በዕለቱ ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ “መንግሥት” በሚል ርዕስ ንግግር ያቀርብ ነበር። ውብ በሆነው በኢሪ ሐይቅ በሚገኘው አዳራሽ ውስጥ 8,000 ገደማ ተሰብሳቢዎች ይህን ንግግር ለማዳመጥ ታደሙ።
ወንድም ራዘርፎርድ ለ90 ደቂቃ ንግግር ከሰጠ በኋላ የንግግሩ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደረሰ፤ ክርስቶስ መንገሡን ያምኑ እንደሆነ ድምፁን ከፍ አድርጎ ለአድማጮቹ ጥያቄ አቀረበ። የተሰበሰበው ሕዝብ በሚያስገመግም ድምፅ አዎንታውን ገለጸ። ወንድም ራዘርፎርድ አክሎ እንዲህ አለ፦ “እናንተ የእሱ አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁ። ስለዚህ ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ!” ይህን ተከትሎም አንድ ትልቅ ሸራ ተተረተረ፤ “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ” የሚል ማስታወቂያ ተጽፎበት ነበር።
ተሰብሳቢዎቹ የተላለፈውን የስብከት ጥሪ ሲሰሙ የአገልግሎት ቅንዓታቸው ተቀጣጠለ። ከአድማጮች መካከል አብዛኞቹ ቀድሞውንም በስብከቱ ሥራ ይካፈሉ ነበር፤ ሆኖም የወንድም ራዘርፎርድ ንግግር ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት መልክ መልክ እየያዘ በነበረበት በዚያ ወቅት በጥረታቸው እንዲገፉበት አበረታቷቸዋል። በወቅቱ በ20ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ትገኝ የነበረችው እህት ኤተል ቤነኮፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ከዚህ ስሜት ቀስቃሽ ንግግር በኋላ የተሰማቸውን ስሜት ስትናገር “ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ [ልባቸው] በቅንዓትና በፍቅር ተሞልቶ ነበር” ብላለች። በ1922 የ18 ዓመት ወጣት የነበረችው ኦዴሳ ታክ ደግሞ “‘እነሆኝ! እኔን ላከኝ’ በማለት እንደተናገረው እንደ ኢሳይያስ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ” በማለት ታስታውሳለች።
ወንድም ራዘርፎርድ ንግግሩን ከሰጠ ከሁለት ቀን በኋላ የዓለም አቀፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር የአቋም መግለጫ አሳለፈ። መግለጫው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ጌታችንን እና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝና ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረገ የክርስቲያኖች ቡድን መጠን በጦርነት፣ በአብዮት፣ በነውጥ ወይም በማንኛውም ዓይነት ዓመፅ መካፈልን እናወግዛለን፤ የአምላክን ቃል አላግባብ በመጠቀም ሰዎችን የሚበዘብዙና የሚያጭበረብሩ ሰዎችን ድርጊት አጥብቀን እንቃወማለን። ልባዊ ፍላጎታችን ሰላም ነው።” ይህ መግለጫ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት እጃቸውን ካስገቡትና ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ይህን ድርጊታቸውን ከደገሙት ሌሎች ሃይማኖቶች ምን ያህል እንደሚለዩ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነበር።
የሰኔ 15, 1922 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “በ1922 የሚደረገው አጠቃላይ ስብሰባ እስከ ዛሬ ከተደረጉት ሁሉ እጅግ የላቀ እንደሚሆን እንጠብቃለን፤ ይህ እንዲሳካም በሁሉም አቅጣጫ ጥረት እየተደረገ ነው። . . . በስብሰባው ላይ ለሚገኙት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የማይረሳ ትዝታ ጥሎባቸው እንደሚያልፍ እናምናለን።”
በእርግጥም ስብሰባው የታለመለትን ግብ አሳክቷል። ይህ ከሆነ ከመቶ ዓመት በኋላም ንጉሡንና መንግሥቱን ለማስታወቅ የሚከናወነውን ሥራ ይሖዋ እየባረከው እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነው።—ማቴዎስ 24:14