ሚያዝያ 27, 2020
ዩናይትድ ስቴትስ
የ2020 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—በዩናይትድ ስቴትስ
በሁለት ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የመታሰቢያው በዓል ንግግር ተሰራጨ
በፓልም ቢች ካውንቲ፣ ፍሎሪዳ በሚገኙ ሁለት ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ሚያዝያ 7 ምሽት ወንድሞች ተገኝተው ንግግር መስጠት ባይችሉም ከ1,100 የሚበልጡ ታራሚዎች አስቀድሞ የተቀረጸውን የመታሰቢያውን በዓል ንግግር አዳምጠዋል።
በየሳምንቱ ወደ ማረሚያ ቤቶቹ ሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጡት 12 ወንድሞች መካከል አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ነገር የተመቻቸበት መንገድ በጣም አስደንቆናል። ይሖዋ እነዚህ ሰዎች የመታሰቢያውን በዓል ንግግር እንዲሰሙ እንደፈለገ ግልጽ ነበር።”
ወንድሞች በእነዚህ ሁለት ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የመታሰቢያው በዓል እንዲከበር ለማድረግ የማረሚያ ቤቱን ቄስ ፈቃድ ጠይቀው ነበር። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተለያዩ ገደቦች ከተጣሉ በኋላ ግን ይህ ሐሳብ ቀረ። ወንድሞች አማራጭ ከመፈለጋቸው በፊት ቄሱ የመታሰቢያውን በዓል የተቀረጸ ንግግር ማሳየት ይቻል እንደሆነ ሲጠይቃቸው ወንድሞች በጣም ተገረሙ። ቄሱ ንግግሩን በሁለቱም ማረሚያ ቤቶች ለማሰራጨት ዝግጅት ጀምሮ ነበር።
ወንድሞች የመታሰቢያው በዓል መጋበዣ በማረሚያ ቤቶቹ እንዲሰራጭ ወይም እንዲለጠፍ ሲሉ ከቪዲዮው ጋር አብረው መጋበዣ ወረቀቱን ለቄሱ ሊልኩ አስበው ነበር። ሆኖም ቄሱ የመታሰቢያውን በዓል ንግግር የሚያስተዋውቅ ፖስተር ማረሚያ ቤቱ ውስጥ ለጥፎ እንደነበር ሲሰሙ አሁንም በጣም ተገረሙ። የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ምሽት ላይ ሁሉም እስረኞች ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ማዳመጥ ይችሉ ነበር።
ከመታሰቢያው በዓል በኋላ የማረሚያ ቤቱ ቄስ ለእስረኞቹ የሚሆን ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲልኩለት ወንድሞችን ጠየቃቸው። በማረሚያ ቤቱ የተቀመጡት መጽሐፍ ቅዱሶች በሙሉ ቢሰራጩም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ ተጨማሪ እስረኞች ነበሩ።
የአምላክ ቃል ወደ ሰዎች እንዳይደርስ እስር ቤትም እንኳ ሊያግደው እንዳልቻለ ማወቃችን በጣም አስደስቶናል።—ማቴዎስ 24:14