ሐምሌ 22, 2019
ዩናይትድ ስቴትስ
ደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ባሪ በተባለ አውሎ ነፋስ ተመታ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 13, 2019 ውቅያኖስ ላይ የተነሳ ከፍተኛ ማዕበልና አውሎ ነፋስ ወደ ሉዊዝያና ሲደርስ ኃይሉን ቀንሶ ባሪ የሚባል አውሎ ነፋስ ሆነ። አውሎ ነፋሱ በሉዊዝያና፣ በሚሲሲፒና በአላባማ ግዛቶች ብዙ ቤቶችን አፈራርሷል እንዲሁም የጎርፍ አደጋና የኃይል መቋረጥ አስከትሏል።
በአደጋው ሕይወቱን ያጣ ወይም የአካል ጉዳት የደረሰበት አስፋፊ ባይኖርም 123 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። በተጨማሪም አውሎ ነፋሱ በ97 የወንድሞቻችን ቤቶችና በ5 የስብሰባ አዳራሾች ላይ ጉዳት አድርሷል።
የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎች በአደጋው ለተጠቁ አስፋፊዎች እረኝነት እያደረጉ ነው። በተጨማሪም በጎረቤት ጉባኤዎች ያሉ አስፋፊዎች ውኃ፣ ምግብና መጠለያ አቅርበዋል። የተጎዱ ቤቶችን የመጠገኑን ሥራ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ባሪ የተባለው አውሎ ነፋስ ካስከተለው አደጋ ጋር እየታገሉ ያሉትን በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንደግፋቸዋለን እንዲሁም በጸሎታችን እናስባቸዋለን።—ምሳሌ 18:10