መስከረም 18, 2019
ዩናይትድ ስቴትስ
ዶሪያን የተባለው አውሎ ነፋስ ያስከተለው ጉዳት
ዶሪያን የተባለው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ በባሃማስ ደሴት ላይ ጉዳት ካደረሰ በኋላ በምሥራቅ በኩል የሚገኘውን የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ጠረፍ መታ። ዓርብ መስከረም 6, 2019 አውሎ ነፋሱ በኬፕ ሃተራስ፣ ኖርዝ ካሮላይና ያለፈ ሲሆን በዚያም በቤቶችና በሱቆች ላይ ጉዳት ያደረሰ የጎርፍ መጥለቅለቅ አስከትሏል። መስከረም 7, 2019 ደግሞ በኖቫ ስኮሻ፣ ካናዳ ኃይለኛ ነፋስ አስከትሏል።
የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ሪፖርት እንዳደረገው በባሃማስ ከሚኖሩት 1,742 አስፋፊዎች መካከል አንዲት እህት መጠነኛ ጉዳት ደርሶባታል። ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ 48 የይሖዋ ምሥክሮች ቤቶች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 8 ቤቶች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።
በግሬት አባኮ ደሴት የሚኖሩት ብዙዎቹ አስፋፊዎች አካባቢያቸውን በመልቀቅ የባሃማስ ዋና ከተማ ወደሆነው ወደ ናሶ ሄደዋል። በዚያም ወንድሞችና እህቶች አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ መጥተው ሞቅ ያለ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴውና የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በአደጋው ለተጎዱት ወንድሞች እርዳታ የመስጠቱንና እረኝነት የማድረጉን ሥራ እያደራጁ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚሠሩ ወንድሞችም እርዳታ ለማበርከትና ለጉባኤዎቹ መንፈሳዊ ማበረታቻ ለመስጠት አደጋው ወደደረሰበት አካባቢ ሄደዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አውሎ ነፋሱ በዋነኝነት ጉዳት ያደረሰው በኖርዝ ካሮላይናና ሳውዝ ካሮላይና ግዛቶች ላይ ነው። በአደጋው የተጎዱ ወንድሞችና እህቶች ባይኖሩም 737 ወንድሞቻችን ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፤ አብዛኞቹ መኖሪያቸውን ለቀው የሄዱት ወደ ቤታቸው መመለስ እስኪችሉ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ብቻ ነው። በተጨማሪም 50 ቤቶችና 12 የስብሰባ አዳራሾች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በካናዳ ከሚኖሩ ወንድሞቻችን መካከል ጉዳት የደረሰበት የለም። አውሎ ነፋሱ በአንዳንድ ወንድሞቻችን ቤቶች ላይ አነስተኛ ጉዳትና የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ አስከትሏል። በአካባቢው ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ለወንድሞቻቸው እርዳታ አበርክተዋል።
ይሖዋ እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ጊዜ በእሱ የሚታመኑ ወንድሞች ‘እርዳታ ለማግኘት ያቀረቡትን ልመና’ ስለሰማቸው እናመሰግነዋለን።—መዝሙር 28:6