በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መስከረም 5, 2019
ዩናይትድ ስቴትስ

ዶሪያን የተባለው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ ባሃማስን አወደመ

ዶሪያን የተባለው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ ባሃማስን አወደመ

በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ከተነሱት በጣም ኃይለኛ አውሎ ነፋሶች አንዱ የሆነው ዶሪያን የተባለው አውሎ ነፋስ እሁድ መስከረም 1, 2019 በሰሜናዊ ባሃማስ በሚገኘው ግሬት አባኮ ደሴት ላይ ደረሰ። ዶሪያን በዝቅተኛ ፍጥነት የሚንቀሳቀስ እንዲሁም ኃይለኛ ነፋስና ዝናብ የቀላቀለ መሆኑ ይበልጥ አደገኛ አድርጎታል። አውሎ ነፋሱ በሊዋርድ ደሴቶች፣ በፖርቶ ሪኮና በቨርጅን ደሴቶች ሲያልፍ ይህ ነው የሚባል ጉዳት አላደረሰም።

የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ አውሎ ነፋሱ በወንድሞቻችንና በቅርንጫፍ ቢሮው ንብረቶች ላይ ያስከተለውን ጉዳት በተመለከተ መረጃ እያሰባሰበ ነው። በግሬት አባኮ ደሴት በድምሩ 46 አስፋፊዎች ያሏቸው ሁለት ጉባኤዎች ያሉ ሲሆን እስካሁን ባለን መረጃ መሠረት ጉዳት የደረሰበት አስፋፊ የለም። ሆኖም በደሴቱ ላይ ያለው ብቸኛ የስብሰባ አዳራሽ ወድሟል።

በግራንድ ባሃማ ደሴት ውስጥ አራት ጉባኤዎችና 364 አስፋፊዎች ይገኛሉ። እስካሁን ያለን መረጃ እንደሚያሳየው 196 ወንድሞች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን 22 ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሦስት ቤቶች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።

አውሎ ነፋሱ ከመድረሱ በፊት ቅርንጫፍ ቢሮው በአደጋው በተጠቁት አካባቢዎች ለሚገኙት የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎች መመሪያ አስተላልፎ ነበር። ቅርንጫፍ ቢሮው ሁሉም ወንድሞች ወደ ዋና ከተማው ወደ ናሶ ወይም መጠለያ ወዳለባቸው ሌሎች ቦታዎች እንዲሄዱ ሐሳብ አቅርቦ ነበር።

በአውሎ ነፋሱ ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንጸልያለን። ይሖዋ የደረሰባቸውን ችግር እንደሚያይና ይህን የጭንቅ ጊዜ ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ብርታት እንደሚሰጣቸው እንተማመናለን።—መዝሙር 46:1, 2