ግንቦት 12, 2020
ዩናይትድ ኪንግደም
እንግሊዝ የይሖዋ ምሥክሮች የሃይማኖታቸው አባል የሚሆነውን ሰው የመወሰን መብት እንዳላቸው አረጋገጠች
መጋቢት 17, 2020 የእንግሊዝና የዌልስ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ ምክንያት የተጠየቀን ይግባኝ ውድቅ አደረገ፤ ቀደም ሲል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ውገዳ የሚሰጠውን መመሪያ የመተግበር መብታችንን የሚያስከብር ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ ጉባኤዎች አንድ ግለሰብ የይሖዋ ምሥክር እንዳልሆነ ማስታወቂያ ማስነገራቸው ሕገ ወጥም ሆነ የግለሰቡን ስም እንደማጥፋት የሚያስቆጥር አለመሆኑን ገልጿል። የፍርድ ቤቱ ዳኛ የሆኑት ሪቻርድ ስፒርማን ውሳኔያቸውን ሲያስተላልፉ እንዲህ ብለዋል፦ “በቅዱሳን መጻሕፍት ሕጎች የሚመራ አንድ ሃይማኖታዊ ቡድን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ አንድን ኃጢአተኛ የማስወገድ መብት ሊኖረው ይገባል። ይህ ምክንያታዊ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ነው፤ ምክንያቱም የቅዱሳን መጻሕፍትን ሕጎች ለመታዘዝ ያልቻለ ወይም ፈቃደኛ ያልሆነ ሰው የሃይማኖታዊ ቡድኑ አባል ሆኖ መቀጠሉ ተገቢ ካለመሆኑም በተጨማሪ እንዲህ ያለው ሰው ካልተወገደ በታማኞቹ አባላት ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።”
ከሳሹ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲቀለበስ ለማድረግ ሲል ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን አቀረበ። ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ግን ይግባኙ “መሠረተ ቢስ” እንደሆነ በመግለጽ ውድቅ አድርጎታል፤ በተጨማሪም የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ‘ምንም ስህተት እንደሌለውና አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባላቱን የማስወገድ ሥልጣን ሊኖረው እንደሚገባ’ ገልጿል።
የይሖዋ ምሥክሮች ጠበቃ የሆነው ሼን ብሬዲ ስለ ውሳኔው ሐሳብ ሲሰጥ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ውሳኔ በርካታ የእንግሊዝ ፍርድ ቤቶች፣ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት እንዲሁም በካናዳ፣ በአውሮፓና በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ካስተላለፏቸው ውሳኔዎች ጋር የሚስማማ ነው። እነዚህ ሁሉ ውሳኔዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሃይማኖታቸው አባል የሚሆነውን ሰው የመወሰን መብት እንዳላቸው ያረጋግጣሉ።”
ፍርድ ቤቱ የጉባኤዎቻችንን መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ለመከተል መብታችን እውቅና በመስጠቱ ደስተኞች ነን።—1 ቆሮንቶስ 5:11፤ 2 ዮሐንስ 9-11