ጥቅምት 21, 2022
ዩናይትድ ኪንግደም
የማቴዎስ መጽሐፍ በፑንጃብኛ (ሻህሙክሂ) ቋንቋ ወጣ
ጥቅምት 9, 2022 የብሪታንያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ፖል ኖርተን መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በፑንጃብኛ (ሻህሙክሂ) ቋንቋ መውጣቱን በቀጥታ በተላለፈ ፕሮግራም ላይ አስታወቀ። በብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ባሉ የስብሰባ አዳራሾች ተገኝተው ስርጭቱን በቀጥታ የተመለከቱትን ጨምሮ ከ1,300 የሚበልጡ ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለውታል። መጽሐፉ በድምፅ፣ በኤሌክትሮኒክ ፎርማትና በወረቀት ወዲያውኑ ወጥቷል።
በሕንድና በፓኪስታን ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሁም በሌሎች አገራት ያሉ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ፑንጃብኛ ይናገራሉ። በጉርሙኪ የፊደል አጣጣል የተጻፈው ሙሉው ፑንጃብኛ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅምት 2020 መውጣቱ ይታወሳል። አሁን የወጣው ይህ ትርጉም የተዘጋጀው ግን ፑንጃብኛን በሻህሙክሂ የፊደል አጣጣል ለሚያነቡ ሰዎች ነው፤ እነዚህ ሰዎች በጥቅሉ ሲታይ የጉርሙኪን የፊደል አጣጣል ማንበብ አይችሉም ወይም አንዳንዶቹን ቃላት አያውቋቸውም። በፑንጃብኛ (ሻህሙክሂ) የሚያነቡ ሰዎች እስከ ዛሬ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ኡርዱ ባሉ ሌሎች ቋንቋዎች ለማንበብ ይገደዱ ነበር።
ባለፉት ዓመታት የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ወደ ፑንጃብኛ (ሻህሙክሂ) ለመተርጎም የተደረጉ ጥረቶች ነበሩ። የዚህ የማቴዎስ ትርጉም አዘጋጆች ግን ልዩ ጥረት ያደረጉት ለማንበብና ለመረዳት ቀላል የሆነ ትርጉም በማዘጋጀት ላይ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ ትርጉም የይሖዋን ስም ይዟል።
በሥራው የተሳተፈ አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች የይሖዋን ስም በቤተ ክርስቲያን ዝማሬ ላይ ሰምተውት ይሆናል። ሆኖም ተርጓሚዎች ከአብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ይህን ስም ስላወጡት ሰዎች ወደ አምላክ መቅረብ እንዲቸገሩ አድርገዋል። አሁን ይህን የማቴዎስ ትርጉም ሲያነቡ የአምላክን ስም መጀመሪያ በነበረባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ ተጽፎ ያገኙታል።”
ይህ ትርጉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡና ስሙን እንዲያወድሱ እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።—ማቴዎስ 6:9